የብርቱካን ተረት!

“ደሀ ተበድሎ ማሩኝ ይላል ቶሎ”

ዝምቧ አንድ በሬ ግንባር ላይ አርፋ ቀኑን ሙሉ እዚያው ትውላለች። አመሻሹ ላይ መሄድ ፈለገችና በል አንግዲህ አያ በሬ መሄዴ ነው ደህና እደር ትለዋለች። አያ በሬም ግርም ብሎት ለመሆኑ መቸ መጥተሽ ነው ከምኔው የምትሄጂው አላት። እሷ እንደዚህ አብረን ውለናል ብላ ስትዘባነን ትልቁ በሬ ግን ላዩ ላይ አርፋ የዋለችውን ዝምብ አላስተዋላትም! እንዴት አድርጎ!

ዶ/ር ያዕቆብ የሚባሉም “ፖለቲከኛ” ሰሞኑን (ብርቱካን ስለተፈታች) “አሁን እሷ በፈለገችኝ ቦታ ተሰማርቼ ለመስራት ወደ ፖለቲካው እመለሳሁ” ብለዋል። አይ መከራችን! ለካ እሳቸውም እስካሁን ፖለቲካው ውስጥ ነበሩ። ለካ ባለፈው… “ከፖለቲካው ዓለም ወጥቻለሁ፣ እንደ ኢህአዴገ ሁሉ እኛም ተቃዋሚዎች በወጣቶች መተካት ይኖርብናል…” ብለው የተናገሩት በብርቱካን መታሰር አኩርፈው ነው። ስለዚህ አልታወቀላቸውም እንጂ ከሷ ጋር ሲሰቃዩ፣ ሲንገላቱ፣ እሷን ለማስፈታት ሲታገሉ ኖረዋልና አሁን ወደ ፖለቲካው ዓለም “ይመለሳሉ” ማለት ነው። ቀድሞውንም ቢኖሩበትማ አይመለሱም ነበር። ደግሞስ ስትፈታ እንጂ ስትታሰር ያልፈለጓት ሴት ምን ታደርግላቸዋለች? ህዝብ እንዲህ መጫወቻ ሆኖ ቀረ? ለማንኛውም ከበሬው ጋር እንደዋለችው ዝምብ “እሽ!” ከማለት ሌላ ምን ምርጫ ይኖራል! ብርቱካን ላይ የሚንጠለጠለው በዛ!

ብርቱካንን ለመቀበል ብዙ ሰው ቤቷ ድረስ ሄዶ ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን ዶ/ር ነጋሶ አቶ ስዬ አብርሃ ኢንጂነር ግዛቸውን ጨምሮ ብዙ የፖለቲካ ሰዎች ነበሩ። ድርጅቷን እንደቅርጫ ተከፋፍለው፣ በነገር ታስረው ሲባሉ የከረሙት ፖለቲከኞች፣ በመፈታቷ የተፈቱ “ሆነው” ቤቷ ተገኙ። ባይከፋፈሉ ናሮ አንድነት የተባለው ድርጅቷን ሁለት ቦታ አይከፍሉትም ። ጠንክረውና አገር አስተባብረው የአፈታቷንም መልክ ሌላ ገጽታ ባስያዙት ነበር። ወይ ከምርጫው ወይ ከእርግጫው ሳይሆኑ ነገሩን ሁሉ እንዲህ ካበለሻሹት በኋላ አሁን ደግሞ እሷን ለሁለት ለመክፈል የየአንጻራቸውን ሤራ እያንሾኳሾኩባት ይመስላል። ከእስር ቤት ወጥታ እንኳ ማረፊያ ድርጅት ያሳጧት እነዚህ ሰዎች በፊቷ እየተሳሳቁ ሲያወሩ ፍቅር ያላቸው ይመስላሉ።

እሷም የዋዛ አይደለችምና “ፖለቲካውን ለመቀጠል ሁኔታዎችን እስካጠና ድረስ ትንሽ ጊዜ እወስዳለሁ” ብላለች። ጊዜው ምን ያህል እንደሆነ ማሰብ የማይቀር ቢሆንም ማጠደፉም የሚሆን አይደለም። በሌላም በኩል ጽናቷ የሚደነቅ ቢሆንም አመራሯ የሚናፈቅ እንደ አስፈላጊነቱም የሚጠየቅ መሆን ይኖርበታል። ሁሉንም ነገር ከሷ ጋር ብቻ አቆራኝቶ ነገር ዞር ያለ እንደሆን የዓለም መጨረሻ አድርጎ ከመሸበር እንቁላሎችን ሁሉ አንድ ቅርጫት (ብርቱካን) ውስጥ ብቻ መክተት አደጋ አለው። መሪያችን! ጀግና! ማንዴላ… የተባሉ ብዙ ሰዎቻችን እየመጡ ሄዳዋል። ይህ ደግሞ አንድም ለኛ አንድም ደግሞ አብዝተን ለምናስጨንቃት ብርቱካን ሚደቅሳ ጥሩ አይደለም። ድክመቷን ስንፈቅድ፣ ልጅነቷን ስናስተውል፣ የደረሰባትን ግፍ ሁሉ ስናስብላት፣ የተሰጣትንም ማስፈራሪያና ስውር ማስጠንቀቂያ…ስንገምት ትንሽ ለቀቅ እናደርጋታለን። በተመለደው ጭካኔያችን (ድሮም እኮ እሷ…እያልን) ነገ አውርደን ከምንፈጠፍጣት ጀግናም ብትሆን ሰው መሆኗን አውቀን ልንጠነቀቅላት ይገባናል። አይዞሽ ብለናት ከድቅድቅ ጨለማ አስጥለናት ተኝተን ያደርን ሰዎች “እንዲህ ብታደርግ እንዲያ ባታደርግ” ከሚል ስሜት አልባ ወሬ ፈቀቅ ብንል ጥሩ ነው። “መለስን ፈርቶ ብርትኳንን” እንዳይሆን ትችቱን አነስ ውዳሴውን ቀነስ ማድረግ ያስፈልገናል። ከእስር ወጥታ እስር እንዳትገባ ነጻነቷን እንስጣት! እስኪ ፀሐይቱንም ትንሽ አይታ ትጠግብ!

ይልቁንም ካሁን በኋላ ጨርሶ እንዳትነሳ አድርገው ሊመቷት የሚችሉትን የአምባገነኖቹን ቀጣይ ሤራና ፕሮፖጋንዳ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባናል። ለምሳሌ ብርትኳን ሚደቅሳ የፈለገችውን ዓይነት የይቅርታ ደብዳቤ ብትጽፍ “የውጭ አገር መንግሥታት ያስፈቱኛል…ብዬ” እያለች አትጽፍም። ይህ ዓይነቱ ክርክር ነገ ሊነሳ ይችላል። ይህ ሊመጣ መቻሉን የሚያውቀው መልቲው መንግሥት ብርትኳን በእጇ የጻፈችውን ጽሑፍ አውጥቶ ሊለጥፍ ይችላል። ምክንያቱም ከይቅርታው በስተጀርባ የአፈጻጸም ሚስጥር መኖሩ ይገመታል። ለምሳሌ መጀመሪያ ጽሑፍ ይላክላታል። የተላከላትን ጽሑፍ በእጅ ጽሁፏ ገልብጣ እንድትጽፍ ትደረጋለች። ያንን ወስደው ለክፉ ቀን ያስቀምጡና በታይፕ የተመታውን እንድትፈርመው ያስድርጓታል። ብርቱካን የምትገደደው ሁለት ጊዜ ሊሆን ይችላል። አንድ በእጇ እንድትገለብጥ ሁለተኛ እንድትፈርም። ከዚህ በኋላ ምን አንደበት ይኖራታል?

“ቀድሞ ነገርስ ለምን ትፈርማለች?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። እንደዚያ ያለ የፌዝ የይቅር ታ ደብድቤ እያለቀሰች ሳይሆን እየሳቀች የማትፈርምበት ምክንያት ምን ይኖራል? በዚያ ላይ “ያልተነካ ግልግል ማወቁ” ብቻ ሳይሆን ችግሩ ሰዎቹን አለማወቁ ላይ ነው። ለምሳሌ ከግፎቻቸው ሁሉ በአንድ ወቅት በረሃ እያሉ በፖለቲካ ሀሳብ የተለይዋቸውን የትግል ጓደኞቻቸውን (የግምባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ አባለትን) ማታ ሲያጫውቱ አምሽተው ሌሊቱን በተኙበት ያደረጓቸውን እናውቃለን።  እነሱን አምነው ጧ ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸውን ሰዎች አድብተውና ተጠራረተው በመነሳት በተኙበት የረሸኑ ሰዎች ናቸው። የራሳቸውን ሰው ስዬ አብርሃን እስከነቤተሰቦቻቸው እስር ቤት አጉረው ያደረጉትን አቶ ስዬ ነገረውናል። የራሳቸው ያልሆነቸው ብርቱካንን ለመቅጠፍ ስንት ዓይነት እጅ አላቸው። ለሰዎቹ ታሪክ ሲባል የማይወጣ እየሆነ ነው እንጂ የስንት ሰው ገመና ካሜራ እየጠመዱ አንገት ያስደፉ ጨካኞች መሆናቸውን የምናውቅ እናውቀዋለን። ምሳሌ እማይበቃን ሁሌም አዳዲስ የግፍ ምሳሌ ካላየን እማናምን ሆነን ነው እንጂ ይህንስ መገመት አይቸግረንም። ግፍን በፕሮግራም ነድፈው ከምርጫው በፊት እናስራታለን፣ ልክ ምርጫው አልቆ አቶ መለስ አሸንፈው ካቢያናቸውን ሲመሰርቱ ደግሞ እንፈታታለን… እየተባለ በመዝናናትና በእቅድ የተፈጸመ ግፍ ነው። እንዲህ የሚያሰኝ ግፍ-

“ወደዚያ ስህተት ልገባ የቻልኩት መንግሥት የውጭ ኃይሎችን ተፅዕኖ በመፍራት ሊያስረኝ አይችልም፣ ካሰረኝም ተገዶ በአጭር ጊዜ ይፈታኛል በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። የተሰጠኝን ምህረት በመካድ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግሥትን በማታለሌ ከፍተኛ ፀፀት ተሰምቶኛል። ዳግም በእንዲህ ያለ የማታለል ሥራ እንደማልሳተፍ በማረጋገጥ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥትን ይቅርታ እጠይቃለሁ።”

በዚያ ላይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የኛንም ጭካኔ አንርሳ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ነገ ተነስታ “ተሳስቼ ነበር፣ አቶ መለስ ዜናዊን የሚያህል ታላቅ መሪ መከተል ሲገባኝ…” እያለች ብትናገር… እሷን እንጂ እነሱን እንደማናይ ያውቁታል። ፈጥነን “ሆዳም ከሀዲ ሰላይ!” ማለት እንደምንችል እርግጠኞች ናቸው። እነሱ ያቆስላሉ እኛ እንገድላለን። “የሆነ ነገር አድርገዋት ነው እንጂ ይቺ እኔ የማውቃት ብርቱካን አይደለችም!” የሚል የአንዲት ሰከንድ ምህረት እንደሌለን ያውቁታል። ለነገሩማ ይህን ያህልም መቆየታቸው ህዝባቸውን ስለሚያዉቁ ነው ማለት ይቻላል። የመፈታት እድሏ ዜሮ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ወደ ደግሞ እንደምርጫው 99.6 አሳድገውታል። ብርቱካን ገና በቅጡ አልተፈታችምና መለስ 100 በመቶ ተፈታለች እስኪሉን እንጠብቅ! እኛም ከራሳችን እስር አስቀድመን ብንፈታት ደግሞ በራሱ የ50 ከመቶ ነጻነት ነው።

1 Comment for “የብርቱካን ተረት!”

 1. *********”ደሀ ተበድሎ ማሩኝ ይላል ቶሎ”********

  ከአቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወ-መንፈሳዊ
  አቅሙንም አውቆ፣
  ጊዜውን ደብቆ፤
  ማሩኝ ይላል ቶሎ፤
  ድሃ ተበድሎ ::
  ገፍተውት በሁሉም፣
  ይሙት ዛሬ ቢሉም፤
  ቀምተውት ሀብቱን፣
  ነፃነቱን መብቱን፤
  ወንጀለኛ እያሉት፣
  ለዛሬ እንዳይገሉት፤
  አሁን አቅሙን አውቆ፣
  ጊዜውን ደብቆ፤
  ማሩኝ ይላል ቶሎ፤
  ድሃ ተበድሎ ::
  አዎን”ሁሉም ያልፋል፣
  እስከሚያልፍ ያለፋል፤”
  መባሉን ያወቁ፦
  እንደእነ ብርቱካን ትዕግስት የታጠቁ፤
  በልብ የሰበቁ፤
  ወኔያቸው ያልሞተ፤
  ከውስጥ የሸፈተ፤
  ሕዝብ ሆኖ ይመጣል፣
  ጥቁር ደም ያስምጣል።
  እናም አቅሙን ያውቃል፤
  ድሉን ይጠብቃል።
  እስከዚያው ጊዜ ግን፤
  የማይለቀው ሃቅን፤
  ማሩኝ ይላል ቶሎ፤
  ድሃ ተበድሎ ::

  ለጀግና ብርቱካን ሚደቅሳ

Leave a Reply to Wee-Menfesawe

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios