ህዝቡ ከሥልጣን ይውረድ!

ፖለቲካ ያስጠላል። የሚያስጠላውም በግድ የሚያስፈልግ ነገር ስለሆነ ይሆናል። ፖለቲካ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም ማለት ራሱ ፖለቲካ ነው። የትም አገር ፖለቲካ ጣፍጦ፣ ማር ማር ብሎ አያውቅም። ሰዎች አንድ ነገር ውሸት ነው ወይም ሆን ተብሎ የተጣመመ ወይም የተጋነነ ነገር ነው ማለት ሲፈልጉ “Oh! Come on this is politics,” ይላሉ። ፖለቲካ ቆሻሻ ነገር ነው ብለው በአደባባይ የሚናገሩም ሰዎች አሉ። “Dirty politics!”

ፖለቲካ በራሱ ያስጠላል። የሚያስጠሉ ሰዎች ሲጨመሩበት ደግሞ የበለጠ ያስጠላል። ፖለቲካ ያስፈራል። የሚያስፈራ ምላስ ያላቸው አንዳንድ የተቃዋሚ መደዴዎች፣ በዚያም በኩል መንግሥት አይሏቸው ወስላታ ወንበዴዎች ሲጨመሩበት ደግሞ ፖለቲካ የበለጠ ያስፈራል። “ከዚህ ሁሉ አንተ ታድነኛለህ!” ብታሰርም ታስፈታኛለህ፣ ብሞትልህም ትጮህልኛለህ፣ ልርዳህም ብል ታምነኛለህ ብለው የሚመኩበት ጠንካራ ህዝብ በሌለበት አገር ደገሞ ፖለቲካ እንደኮረንቲ ሲያስፈራ ይኖራል።

ይህ ስጋት አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተሻለ ፖለቲካ በሚያራምዱ አገሮችም ቢሆን ያለ ነው። እነሱ ግን ፖለቲካቸውን “ያስፈራል፤ ያስጠላል” ብለው አይተውትም። ባላቸው ቀዳዳም ቢሆን የሚጠቅመንን ነገር ያደርግልናል ብለው ይሳተፋሉ። አሰቀያሚውን ፖለቲካ ለአስቀያሚ ሰዎች ብቻ አይተውትም። ለአስቀያሚው ፖለቲካ የሚያማምሩ፣ የሚያነጋግሩ፣ የሚደመጡ “ይሄስ ይሁንበት” የሚሏቸው ማጣፈጫ ሰዎች ከመካከላቸው ማውጣት ይችላሉ። እንደኛ አገር መሪ አጣን እያሉ አያለቅሱም!

ለምሳሌ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ደስ ይላሉ። ጥቁርም፣ ሎጋም፣ ወጣትም፣ አንደበተ ርቱእም፣ ስለሆኑ ብቻ እልል ብለው የመረጧቸው እልፍ ናቸው። አፋቸውም ይጣፍጣል። ሽምጥጥ አድርገው ሲዋሹ እንኳ እንደ ቆንጆ ተረት የሚያወሩት ደስ ይላል። ይሄ ለወደዳቸው ነው። ለጠላቸው ደግሞ እንኳን ውሸታቸው ያነጠፉት ወርቃቸው እንኳ አይጥመውም። ምክንያቱም ፖለቲካ ነው። ፖለቲካ ኮተቱ ብዙ ነው። ኢኮኖሚው፣ ዘረኝነቱ፣ ሃይማኖቱ…

“ከኦባማ ቡሽ ይሻለናል” የሚሉትን እነ ሳራ ፔለንን እያየን ነው። ሰው እንዴት ሳራ ፔለንን ይደግፋል? ብለን ስንገረም “መለስን እንደግፋለን!” የሚሉ ሰዎች ተሰልፈው ስናይ መልስ ይሆነናል። “ልማታዊ አምባገነንነትን እንደግፋለን! ባልና ሚስት የሚገዟትን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንደግፋለን! እያሉ የሚጮኹት “ሚዛናዊ ሊቃውንት” እነመለስ ይበልጥ እንዲጠሉ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው መቸም የማይካድ ነው። ችግሩ መለስ ለምን ተደገፉ ሳይሆን እንዴትና በማን ተደገፉ የሚለው ሲታሰብ ነው። እንኳን ለሌላው ለአቶ መለስ ራሳቸው ደጋፊዎቻቸው ቋቅ ሳይሏቸው አይቀሩም። ከማይሆን ድጋፍ ሞገስ ያለው ነቀፌታ ይሻላል።

የንግግር መብት ግን ትንሽና ትልቅ ሳይል ለምናምንቴዎች ሁሉ የተገባ ነውና ለምን ደገፉ፣ ለምን ተሰለፉ ብሎ ማለት እንደነሱ መሆን ነው። በዚያ ላይ “እንኳንም ገደልክልን፣ ጨምረህም ግደልልን! እየያዝክ እስረልን፣ ደግሞ እንኳንም አገር አስገነጠልክልን፣ እንኳንም ለያየኸን፣ ከናድከው አገር ያቆምከው ፎቅ ይበልጣል…” እያሉ የሚያላዝኑ ምናምንቴዎች ፖለቲካን እንዴት እንደሚያቆሽሹት ማሰብ እንችላለን። በወዲሁም ያገኙትን ሁሉ ማንዴላችን፣ በወረት ያሸበረቁትን ሁሉ “መሪዎቻችን” ማለት እንደሚወዱና ወዲያው ደግሞ ፈጥነው የካቡትን አሽቀንጥረው እንዲሚያዋርዱ ተቃዋሚዎች ማለት ነው። የእነሱን ዘለፋና ዘግናኝ ውርጅብኝ በቀኝ ጆሮ፣ ጨምላቃ የበሰበሰ ጨርቅ ወራዳ ምንትስ እያለ አፉን እንዳመጣበት የሚከፍተውን መለስ ዜናዊን ደግሞ የአፍሪካ መሪ ሊያደርጉ የሚጥሩ ለፋፊና ቀፋፊዎችን ደግሞ በግራ ጆሮ እየሰሙ መኖር ግዴታ ነው። እድሜ ለመብትና ለፖለቲካ!

ፖለቲካ ብዙ ጊዜ ወይ መጥላት ወይ መውደድ እንዲሆን የሚያደርጉት እንደዚህ ያሉት ግራና ቀኞች ናቸው። ፖለቲካ በራሱ ወይ መደገፍ ወይ መቃወም ነው። ማንንም ሳያስቡ ስለ አንድ ነገር በተናገሩ ቁጥር አንድ ሌላ ሰው ሊያስቀይም ይችላል። የትኛውም አሰተያየት የሌላውን ሰው አስተያየት የሚቃወም መሆኑ የግድ የሆነበት ነገር ቢኖር ፖለቲካ ነው። አንዱን መደገፍ ማለት ሌላውን መቃወም ነው። ሌላውን መቃወም አንዱን መደገፍ ይሆናል። በፖለቲካ የግል አስተያየት የሚባል ነገር የለም። ሁሉ ነገር የቡድን ነው። ሰዎች ይሄ ከማንም ሳልማከረው በራሴ የደረስኩበት የግሌ አቋም ነው እያሉ ምለው ቢገዘቱም አይሰራም። አድማጩ ይሄማ የነሱ ወይም የኛ ወገን ነው ለማለት ደቂቃ አይፈጅበትም። ሁሉም ነገር በሁለት የተከፈለ ይመስል መፈረጅ የግድ ነው።

ተፈረጁም አልተፈረጁም ዝምብለው የሚቀባጥሩ ሳይሆን ያለፍረሃት መብታቸውን የሚያስከብሩ ግን ሥልጡንና ብሩክ ህዝቦች ናቸው። በአሜሪካ ኢንዲፔንደንት ነን የሚሉት ይከበራሉ። ምክንያቱም ራሳቸውን አስከብረዋል። “በዚህ በዚህ ዴሞክራቲክ ፓርቲን፣ በዚህ በዚህ ሪፐብሊካንን እመርጣለሁ፤ አሁን ባለሁበት ደረጃ ግን ይህኛው ፓርቲ ጥሩ ነው…” ብለው የመወሰን ምርጫ አላቸው። ወይ ከኛ ጋር ወይ ከነሱ ጋር ብሎ ድርቅና ወይም ብልግና አይደርስባቸውም።

እርግጥ ነው መዘላለፍ በኢትዮጵያውያን አልተጀመረም። በሠለጠኑት አገሮችም ያለ ነው። ፖለቲካ ትብትብና ውስብስብ ነው። አስቂኝና የጅሎች ጨዋታም ነው። አንዳንዴ ኤርትራ አስመራ ላይ ሆነው “አሰብን እናስመልሳለን” እያሉ መግለጫ እንደሚሰጡ ተቃዋሚዎቻችን አስቂኝ ይሆናል። “ሞተንና ተዋግተን ካስገነጠልናት አገር ሰዎች ጋር አየናችሁ፣ አስመራም ተመላለሳችሁ ስለዚህ ከሀዲዎች ናችሁ” የሚሉት የመለስ ደጋፊዎችም እስከነ “ዐይናውጣነታቸው” ይገርማሉ። ያስገነጠለ ቢረሳ የተገነጠለ አይረሳም! ባቀናነው ስድብ መልሰን ስንሰደብ ደስ አይልም።

ፖለቲካ አሳዛኝ፣ አናዳጅ የሚሆንበትም ወቅት ብዙ ነው። ቅጥ ያጣ ባርነት በዝቶ ማንም በውስልትና እየተነሳ፣ – “ከታጋይ ሴቶች ሁሉ አንቺ የተለየሽ ነሽ” የሚላትን ሚስቱን ይዞ፣ አገር እየረገጠ ሊገዛ ሲደላደል ማየቱ ያበግናል። “የደፈረኝን ሁሉ እንደብርቱካን ሚደቅሳ አሰቃይቼ እለቀዋለሁ” እያለ በደካማ ሴት ልጅ ያሳረፈውን ጭካኔ ማለፊያ ድል አድርጎ የሚዘባነን ወንበዴ ያስጠላል። እንዲህ ያለ ግፍ ፊት፣ ፎቅና መንገድ ቀርቶ፣ ወርቅ ቢነጠፍም ፋንዲያ መሆኑ አይቀርም። ልማት በግፍ አይሸቀጥም። ከአናቷ የተቀነጠሰች አገር፣ በተገጣጠመ ፎቅ አትገነባም። “ልማታዊ” ብሎ ቋንቋ ምንድነው? እንደው ጨዋ እንሁን እየተባለ አንደበት ሲለጎም ንቀታቸው አናት ላይ እየወጣ ነው!

ደግሞም ህገመንግሥት መቀበል ምንትስ ይባላል? ኢትዮጵያ ውስጥ ህገመንግሥቱ ይከበር ማለት ፀረ ህገመንግስት ሊያስብል ይችላል። ወይም መንግሥትን በኃይል ለመጣል መሞከር ተደርጎ የሚተረጎምበት መንገድ ሞልቶታል። የኢትዮጵያ ህገመንግሥት እንደ ህልም ነው። ህልምም እንደፈቺው ነው። መንግሥት የፈታውን እየፈታ የሚያስረውን የሚያስርበት ትርጉም አለው።  አቶ መለስ ዜናዊም “ቀይና አረንጓዴ መስመር” ብለው የሚተረጉሙት ነገር አላቸው። በዚህ አምባገነናዊ ትርጉማቸው የሚጠፋውን ጥፋት ሲያስቡት ፖለቲካቸው ያስጠላል።

በዚያ ላይ ምርጫውን 99.6 ከመቶ አሸነፍኩ ሲሉበት ከሳቸው ፖለቲካ ይልቅ ይህን ታግሶ ማደር ደግሞ የበለጠ ያስጠላል። ይሄኮ ተራ ድርቅና ነው። ምናልባትም ትልቅ ብልግና ነው። የሚናቅ ህዝብ ተስፋው ምንድነው? አቶ መለስ ይህን ያደረጉት ደንቆሮ ስለሆኑ ፖለቲካ ስላልገባቸው ነው ማለት ግን አይቻልም። ፖለቲካ እንደ እግርኳስ ጨዋታም ያደርገዋል። ዋናው ግብ ማስቆጠር ነው። ተጠላም ተወደደም አቶ መለስ ዜናዊ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። የፈለጉት ሥልጣን ነው። ሥልጣን ላይ ቆይተዋል። አቀርቅሮ የሚገዛላቸውን ትተን፣ ደጋፊና ተቃዋሚያቸው ነኝ የሚለውን የህዝብ ወገን ብናይ የፖለቲካው ስካር ቁልጭ ብሎ ይታየናል። “የመብት ስካር።” መደገፍም ሆነ መቃወም “መብቴ” ነው የሚባል ባዶ ስካር አለ።

ፖለቲካን አስቸጋሪና አስጠሊታ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ መጥቶም ቀርቶም የሚያስጨንቀው ይሄ ዘልዛላው “መብት” ነው። የመናገር መብት ለሊቅና ለደደቡ፣ ለቅን ሰውና ለአጭበርባሪው እኩል የሚሰጥ ነው። ሰው ስለደገፈውም ሆነ ስለተቃወመው ነገር ከማስረዳት ይልቅ “መብቴ” ነው የሚል ዘጊ መልስ ከሰጠ ምንም ማድረግ አይቻልም። ምክንያቱም መብቱ ነው።  መለስን የሚደግፉ ሁሉ ከሀዲ ሆዳሞች ናቸው ማለት መብት ነው። እንዲህ እያሉ የሚሳደቡ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ መብት ያልገባቸው ደደቦች ናቸው ማለትም መብት ነው። መብት እንዲህ መሆኑ ጥሩ ነው። ግን በአንድ አገር ውስጥ እንዲህ ያለው ነገር ብቻ ሲሰማ የሚውል ከሆነ ፍሬ ነገሩ ምንድነው?

መብት እውቀት አይደለም። እውቀት ማለትም ስለጣፈጠና ስለጎመዘዘ ተመርጦ የሚያዝ አይደለም። የሆነውን በትክክል አመዛዝኖ መገንዘብና እሱ ላይ ተመርኩዞ መጪውን በመገመት መፍትሔ ማመንጨት፣ መንገድ ማመላከት ነው። እንዲሁ ዝምብሎ መቃወምና መደገፍ “መብቴ ነው!” ብሎ መንጣጣት እውቀት አይደለም። ካልተደመጡ መናገር ዋጋው ምንድነው? የንንግር መብት እንደወጠረ ሽንት ሸንቼ ልገላገለው የሚባል ነገር አይደለም። ውጭ አገር ጥንቡን የጣለ ይህ የንግግር መብት አገር ውስጥም ላጭር ጊዜም ቢሆን ኖሮ አይተነዋል። ውሾች ይጮኻሉ ግመሉ ቀጥሏል ተባለ እንጂ የትም አላደረሰም። እንዲያውም ንግግር ብቻ ሰለቸና በቃ ከዛሬ ጀምሮ አፋችሁን ያዙ ተባለ። ህገመንግስታዊ የተባለው የንግግር መብት የሆነው ያልሆነው ሲዘባረቅበት አንድ ነገር ሳይሰራበት በብላሽ ቀረ! ባለመብቱ ህዝቡም አቀረቀረ።

ይህ ህዝብ የሚስማማውን አጥቶ፣ መሪ ቸግሮት፣ ግራ ገብቶት ነው እንጂ… ሁሉም አገሩን ይወዳል…ሲባልም ይሰማል። እውነትነት ቢኖረውም የባሮች ማስተዛዘኛ ሆኖ መቀጠሉ ግን እየታየ ነው። ግራና ቀኝ አይቶ መኪና መንገድ መሻገር የሚችል ጎልማሳ እጄን ይዞ የሚያሻግረኝን እየጠበቅኩ ነው ቢል ማን ያምነዋል? እንዲህ ያለን ምክንያት ከማቅረብ የማይመለሰው ተንሸራታች ህዝባችን ግን በልኬ የተሠራ መሪና ድርጅት አጣሁ የሚል እየመሰለ ነው። ራሱ ያልሠራው መሪና ድርጅት ከየት አባቱ ይመጣለታል?

ፖለቲካ ማሰጠላቱ ካልቀረ እንዲህ ያለው አስጠሊታ ፖለቲካም ቢገባበት ጥሩ ነው። መንግስትም ላይ ተቃዋሚዎችም ላይ ሰልፍ ተደርጓል። አሁን የቀረው ህዝቡ ላይ ነው። ስለዚህ ነጻነት የጠማቸው ጥቂት ሰዎች፣ ባርነትን ፈቅዶ እንቅፋት በሆነው ሰፊ ህዝብ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራት ቢችሉ እንዴት ጥሩ ነበር። መብት መንዘላዘሉ ካልቀረ የዝምተኛው ህዝብ አንደበት ይከፈት! ባርነት ይብቃ! ሥልጣን የህዝብ ነው የሚለው የትም አላደረሰንምና ህዝቡ ከሥልጣን ይውረድ! ህዝብ ይቀየርልን! ህዝብ ሁሉን አዋቂ ነው የሚለው ቀርቶ ማንም የሚነዳው ከብት ነው በሚል መፈክር ይቀየርልን!… እየተባለ ሰልፍ መውጣት ቢቻል ፖለቲካው ትንሽ ጣፈጥ ይል ነበር። ምክንያቱም እንደዚያ ዓይነት ሰልፍ ቢጠራ “አንድ ሰው አይቀርም” ነበር። አይደል?!

ይቺ ናት ፖለቲካ!

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios