“ከኢህአዴግ ጋር ብዙ ጊዜ ተደራድረናል፣ 101 ጊዜ ከድቶናል!”

“እኔ እዚያ ውስጥ ባልገባ ደስ ይለኛል። እኔ እሳቸው (ኃይሉ ሻውልን) ፖለቲካ አውቀው እንዲህ ይበሉ አይበሉ አላውቅም። ምን ትርፍ እናመጣለን ብለው እዚያም ውስጥ እንደገቡ አላውቅም። ለምን ብቻቸውን ተነጥለው እዚያው ውስጥ እንደገቡ እሳቸውን ብትጠይቁ ይሻላል። እነዚያ መሠረታዊ ጉዳዮች ሳይመለሱ ዋስትና ሳይሰጥ መግባታቸው ምክንያቱ አልገባኝም። እናውቀዋለንኮ። ከኢህአዴግ ጋር ብዙ ጊዜ ተደራድረናል፣ 101 ጊዜ ከድቶናል። ለማንኛውም ነገሩኮ ውሎ ሳያድር በሳምንትና ወራት ጊዜ ውስጥ ይታወቃል። ኢህአዴግኮ ካላሳረ፣ ካላባረረ የኢትዮጵያን ህዝብ ማስተዳደር ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል። ይህን እሳቸውም ያውቃሉ፣ እኛም እናውቃለን። እሳቸው እንደሚሉት ታሪካዊ ክንዋኔ ይሁን ሌላ ይሁን ወደፊት እናየዋለን። ፍቅራቸው እንደዚያ ይቀጥል ዳግመኛ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ቲአትር ለመስራት ይሁን በቀናት ውስጥ እናየዋለን። እኛኮ ኢህአዴግ እሳቸው እንደሚሉት ቢሆን ቢያደርግ ደስ ይለናል። ኢህዴግን የሚያውቁ የኢህአዴግ መሪዎች የነበሩኮ እኛጋ አሉ!”

ዶ/ር መረራ ጉዲና

ኖቬምበር 4/2009 ወደ ዋሽንግተን ዲሲ መጥተው የነበሩት የመድረክ እና የኦህኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከዘኢትዮጵያ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

ዘኢትዮጵያ- ስንት ቀን ሆነዎት ከመጡ?

ዶ/ር- መረራ ወደ 10 ቀን እየሆነኝ ነው።

ዘኢትዮጵያ- ለምን መጡ?

ዶ/ር መረራ- ድርጅታችን በየዓመቱ እዚህ እየመጣ ድጋፍ ያሰባሰባል። በዚህ ዓመት ደግሞ የምርጫ ዓመት ስለሆነ ድጋፍ ማሰባሰቡ ለእኛ በጣም ወሳኝ ነው።

ዘኢትዮጵያ- አሁን የመድረክም የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስም (ኦህኮ) ሊቀመንበር ነዎት፤ የትኛውን ወክለው ነው የመጡት?

ዶ/ር መረራ – ሊቀመንበርነቱ የሁለቱም ሊቀመንበር ነኝ። ግን ድጋፍ ለማሰባሰብ የመጣሁት ለኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ ነው። የመድረክ አባሎችን ግን በየቦታው ሳገኛቸው እያነጋገርኳቸው ነው። ሲያትልም ሁለት የመድረክ ደጋፊ ቡድኖችን አነጋግሬያለሁ። እዚህም (ዋሽንግተን ዲሲም) የሚያነጋግሩኝ አሉ። ወደ ሜኔሶታም ሰሞኑን እየሄዳለሁ፣ ተመሳሳይ ሥራ ነው የምሥራው። በመድረክ ስም ግን ስብሰባ አልጠራም። መድረክ ሰፊ ቡድን ስለሆነ ከመጣን አንድ ላይ ሆነን ነው የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርገን ነው መምጣት ያለብን።

ዘኢትዮጵያ- አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በእርስዎ እይታ ምን መልክ አለው?

ዶ/ር መረራ- አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሳየው ባንድ በኩል የገዢው ፓርቲ የመጨረሻ ውጥረት ወይም ምጥ ዓይነት ነገር ይዞት ይታየኛል። የሚመጣው ምርጫ ምን እንደሚሆን ቸግሮታል። ስለሆነም ተቃዋሚውን በአንድ በኩል መደራደር ባንድ በኩል የመከፋፈል ሤራ እያካሄደ ይመስላል። የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ የጠበበበት ሁኔታ ነው ያለው። አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ተብሎ የሚገመት አይመስለኝም። ገዢው ፓርቲ ሳያስር ሳያሳድድ ሳያጭበረብር ምርጫውን ለማሸነፍ የሚችልበት ሁኔታ አለ ማለት አይቻልም። ስለዚህ በአንድ በኩል ድርድር፣ በአንድ በኩል ደግሞ ማሠሩን ማሳደዱን የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለውው።

ዘኢትዮጵያ -ምን ያህል ሰው ታስሯል? ለምሳሌ ከእናንተ ድርጅት የታሰረባችሁ ሰው አለ ?

ዶ/ር መረራ- እንዴ አዎ! ባለፈው ወር እንኳ የእኛ ማለትም የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ አባላት ብቻ የሆኑ ከ350 ሰዎች በላይ ታስረውብናል። ስለዚህ ባንድ በኩል ድርድር ይበሉ እንጂ በሌላ በኩል እስሩ ቀጥሏል። በአንድ በኩል አሰረው በሌላ በኩል በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንድትደራደር ይጠይቁሃል። አንዳንዶችም ይህን ሁኔታ ተቀብለው ይፈራረማሉ።

ዘኢትዮጵያ- ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ምን ሊፈጥር ምን ሊያመጣ ይችላል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር መረራ- እንግዲህ እኔ ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄዳቸው ነው የሚታየኝ። ውጥረቱ እየሰፋ ነው። የፖለቲካ ሙቀቱ ወደላይ እየወጣ ነው። ምን ሊፈጥር እንደሚችል ለመገመት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሁኔታዎች በጣም ከፍተዋል። ኢህአዴግ ይህን ሊወጣበት ከማይችልበት አስቸጋሪ ውጥረት ውስጥ ነው ያለው።

ዘኢትዮጵያ- ይሄ ሁል ጊዜ ይባላል። ከዚህም በፊት ተብሏል። “አልቆለታል ፣ በቃው!” የማለት ነገር በየጊዜው ይሰማል። ሆኖ የታየ ነገር ግን የለም። ያሁኑን “አልቆለታል”ከበፊቱ “አልቆለታል” የተለየ የሚያደርገው ምንድነው? ኢህአዴግን ምን የሚያስገድደው ነገር አለ ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር መረራ- እንግዲህ ምንድነው ያሉትን ሁኔታዎች ማየት ይገባል። በራሳችን የፖለቲካ ግምገማ ከተለያዩ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያለው ግንኙነት ምንድነው? መንግሥት የሚሠራቸው ነገሮች ውጤታቸው ምንድነው? ከገበሬው ጋር ያለው ግኑኙነት ምንድነው? ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ከገበሬው ጋር ማዳበሪያ በካሽ ካልገዛችሁ ብድር አልሰጣችሁም ማለቱ ገበሬውን ማደበሪያ መከልከሉ አስኮርፏል። ወጣቶች ለምሳሌ የእነሱ አባል ካልሆኑ ሥራ እንዳያገኙ መንግሥት ፖሊሲ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። ረሀቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን እየነካ ነው። ኑሮ ውድነቱ በጣም አስቸጋሪ በሆነ መንገድ እየተሰቀለ ነው። የነዳጅ ዋጋ ንረት እንደዚሁ በሌሎች ሸቀጦችና የምግብ እህሎች ላይ ከፍተኛ ውድነት አስከትሏል። ለምሳሌ ጠፍ ድሮ 200 ብር በታች የነበረው አሁን ወደ 1ሺ200 አካባቢ ነው። ስለዚህ ይሄ መንግሥት ለኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ሠርቼልሃለው ብሎ በአፉ ሙሉ መናገር የማይችልበት ሁኔታ ነው ያለው። ጧት ማታ እየደጋገሙ ልማት መጥቷል ብልጽግና መጥቷል ኢኮኖሚው አድጓል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተፈጥሯል የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ባዶ መሆናቸውን ህዝቡ እያየ ነው። እነዚህ እነዚህን ስታይ እንግዲህ ከህዝብ የተነጠለ መንግሥት መሆኑ በግልጽ ይታያል። ችግሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በአጭር ጊዜ ለውጥ መፈለግና የሰከነ ሥራ መሥራት አለመስራት ነው። ይሄ እየተሰባሰበ ያለውን የህዝብ ግፊት አቅጣጫ ከማስያዝ ይልቅ ቶሎ ብሎ በአንድ ነገር ላይ የመጣላት የመከፋፈል የመጠላለፉ ነገር አመራርና ትግሉ እንዳይገናኝ አድርጎታል። እነዚያ ነገሮች ከተሟሉ ከምን ጊዜም በላይ የኢህአዴግ መንግሥት ከህዝብ የተነጠለበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስለኛል።

ዘኢትዮጵያ- አሁን የሰጧቸው ምክንያቶች ድሮም የነበሩ ናቸው። መከሰት ከጀመሩ ቆይተዋል። ኢህአዴግና ህዝብ ሁሌም እንደተቃቃሩ ነው። የኑሮ ውድነቱ በፊትም ነበር። ድርቅም በኢህአዴግ እድሜ ውስጥ ተደጋግሞ የመጣ ነው። እነዚህ አሁን የዘረዘሯቸው ነገሮች በፊትም ነበሩ። ከእስከዛሬዎቹ ጋር ሲነጻጸር እድገታቸው ምን ያህል ደርሷል ማለት ይቻል ይሆናል። የዓይነት ሳይሆን የመጠን ሁኔታን ማንሳት ይቻል ይሆናል። ችግሮቹ በኢህአዴግ ላይ አስገዳጅ ሁኔታና ጫና ሊፈጥሩበት ከሚችሉበት ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸው ግን እንዴት ማስረዳት ይቻላል?

ዶ/ር መረራ – በፊት የነበረውና የአሁኑ ግን አንድ አይደለም። ላለፉት አራት ዓመታት የኑሮ ወድነቱ አምስት ስድስት ሰባት እጥፍ ያደገበት ሁኔታ ነው ያለው። አሁን ለምሳሌ ጤፍ ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ሁለት መቶ ብር አካባቢ ነበር። አሁን አንድ ሺ ሁለት መቶ ነው። ለምሳሌ የመንግሥት ሠራተኛ የሆነው ሁሉ መንግሥት በቀን 3 ጊዜ የሚለውን መብላት ቀርቶ አንዴ እንኳ መብላት የማይችልበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው። ገበሬውን ብትወስድ እንደዚሁ ነው። ወደ 13 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የድርቁ ተጠቂ በመሆኑ ረሀብተኛና ተረጂ ሆኗል። ይህን እነሱም ያምናሉ። ግን 7 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ ከረሀብተኛው ክፍል ቀንሰው ሴፍቲ ኔት በሚባለው ፕሮግራም ውስጥ አስገብተው ይቆጥሩታል። እና የረሀቡ ነገር ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሁኔታው ተስፋን የሚያጨለም ነው። ድሮ ከሶስት አራት ዓመት በፊት አባሎቻቸውን ሥራ መቅጠር የተለመደ ነው። አሁን ግን ፊት ለፊት የኢህአዴግ አባል ለሆነ ብቻ ቅድሚያ የሚያሰጥ አሰራር መኖሩ ያልተለመደ ነው። ስለዚህ ነገሮች እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ የመጡበት ሁኔታ አይታይም።

ዘኢትዮጵያ- እርስዎ ያነሷቸው ነገሮች አሉ። ፖለቲካ ድርጅቶች አለመተባበርና ህዝቡን መርቶንና አነሳስቶ ለድል አለማብቃት ነው እንጂ ገዢው ፓርቲ ከህዝቡ የተነጠለበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል። እሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ህዝብ ይህን ሁሉ የኑሮ ውድነትና ጫና ችሎና ተቀብሎ እንዲኖር ያደረገው ምንድነው? ኑሮ ውድነቱን ረሀቡን ተቋቁሞ የሚኖረው እንዴት ነው?

ዶ/ር መረራ- እሱ እንግዲህ የአገሪቱም ባህል ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር ያመጣውን እግዚአብሄር ይመልስልን የማለት ነገር አለ። ስለወደዳቸው ሳይሆን እግዚአብሄር ያመጣብን መቅሰፍት ነው እሱ ይመልሰው ይላል። እንጂ አደጋው ይታያል። ረሃብ እየጎዳው መሆኑ በግልጽ ይታያል። ምንም ጥያቄ የለውም። “የሚበላውን ያጣ ህዝብ ኢህአዴግን መብላቱ አይቀርም!” ብዬ ባንድ ወቅት ተናግሬ ብዙ ችግር ገጥሞኝ ነበር።

ዘኢትዮጵያ- በመንግስት ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ ድርጅቶችም ላይ ቢሆን ተስፋ መቁረጥ እምነት ማጣት ያለ ይመስልዎታል? ለምሳሌ እናንተን የማመን ፍላጎቱ ምን ይመስላል? የናንተስ የመታመን ብቃታችሁ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር መረራ- ህዝቡ ይለያል እኮ! “ማን ከዳኝ ማን አብሮኝ ነው?” ይላል። ለምሳሌ ጥቂት መቶዎች የሚሆኑ አባላት እንኳ የሌላቸው ድርጅቶች አሉ። በመቶሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያሏቸው ድርጅቶች አሉ። የት እንደሚደራጅ፣ ማንን እንደሚደግፍ፣ ማንን እንደሚያምን ይለያል። ሁሉም የፖለቲካ ድርጅት ነኝ ስላለ ሳይሆን ራሱ የሚሳተፍበትን ያውቃል። ስለዚህ ድጋፍ ያላቸው የህዝብ ብሶት ማስተጋባት የሚችሉት ይታመናሉ። ምንም ህዝባዊ ድጋፍ የሌላቸው በኢህአዴግ ኪስ ውስጥ የሚኖሩ ኢህአዴግ ሥር ተሹገጠው የሚኖሩ አሉ እነሱንም ያውቃል።

ዘኢትዮጵያ- የመድረክ አደረጃጀት ቅርጹ ምንድነው? እንዴት ነው የተደራጃችሁት? እንደ ቅንጅት ያለ ነገር ነው?

ዶ/ር መረራ- አዎ ቅንጅት ነው። አደረጃጀቱ እንዳለፈው ቅንጅት ዓይነት ነው።

ዘኢትዮጵያ – ስለዚህ መድረክ ለዚህ ለምርጫ ሲባል የተሰባሰበ ኃይል ነው ብሎ ማሰብ ይቻላል? ወይስ ከምርጫውም በኋላ ሊቀጥል የሚችል ነው?

ዘኢትዮጵያ- እንግዲህ መድረክ ቅንትጅ ነው ሲባል የተወሰነ ሥራ ብቻ ለመስራት የተቀናጀ ነው። ህጉ ውስብስብ ስለሆነ የተወሰነ የጋራ ነገር በጋራ ለመስራት የተሰባሰብን ኃይሎች ነን። በምርጫውም ዙሪያ በአንድ መለስተኛ ፕሮግራም፣ በአንድ ምልክት፣ በአንድ ዓርማ ለመወዳደር ነው። ለምርጫም ብቻ ሳይሆን ምርጫውንም ብናሸንፍ በጥምረት ለመምራት በአንድ ላይ የተሰባሰብን ነው።

ዘኢትዮጵያ – አደረጃጀታችሁ አሠራራችሁ እንዴት ነው? እንቅስቃሴዎቻችሁንም ጨምረው ይግለጹልኝ?

ዶ/ር -አመራር መርጠናል። 65 ገጾች ያሉት መለስተኛ ፕሮግራም አውጥተናል። ያንን ፕሮግራም መነሻ በማድረግ ዋነኛ የአገሪቱ ጉዳዮች ናቸው የተባሉ የፖለቲካ የኢኮኖሚ የማህበራዊና የባህል ጎዳዮች ሁሉ የዳሰስንበት ፕሮግራም (ሚኒመም ማኒስፌስቶ) እያዘጋጀን ነው። እዚህ ላይ ነው እየሠራን ያለነው። እንግዲህ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በላይ ይህን ለማድረግ ስንደራደርና ስንመካከር ቆይተን የ 8 ፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ የሆነውን መድረክ ፈጥረናል። የተለያዩ ማህብረሰብ ክፍሎችን የያዘ ነው። የተለያየ የፖለቲካ ቅርጽና ዓላማ ያላቸውን ኃይሎችን ሁሉ በተወሰነ ደረጃ ያሰባሰበ መድረክ ነው። በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ግዛቶች ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ናቸው ድርጅቶች ያሉበት ነው። ገዢውን ፓርቲ የበለጠ እያደናገጠ የመጣው ይኸኛው ነው። ስለዚህ ከእኛ ውጪ ወይም እኛን ወደ ውጪ በመግፋት ብዙ የፖለቲካ ድጋፍም ሆነ አባላት የሌላቸው ድርጅቶችን መርጧል። ከእነሱ ጋር ተደራድሬያለሁ በሚል፣ ይቺን ጊዜ አልፋታለሁ ብሎ ተነስቷል። ይህ የለመደው አሰራር ነው። አሁን ስምምነት የተባለው፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ዳግመኛውን የፖለቲካ ቲአትር ለመሥራት ካልሆነ በስተቀር፣ ብዙ የፖለቲካ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። ስለዚህ እኛ መደረክ አካባቢ የተሰበሰብነው ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች መሃል መንገድ ላይ እንዲገናኙ ነው። የገዢውን ፓርቲ የከፋፍለህ ግዛ ሤራ ለመስበር ሁላችንም በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ ሁላችንንም በእኩልነት መርህ፣ ሊያሰተናግድ የሚችል የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። ከሶማሌ ከልል፣ ከደቡብ፣ ከኦሮሞያ፣ ከትግራይ… እያለ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተውጣጡ አባላት ያሉበት ነው። ድጋፍ ከተሰጠን ውጤትና ልዩነት ሊያመጣ የሚችል የፖለቲካ ኃይል የሆነ መድረክ ልንሆን እንችላለን።

ዘኢትዮጵያ- የምትፈልጉትን ድጋፍ እያገኛሁ ነው?

ዶ/ር መረራ- በርግጥ ችግር ይኖራል። ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚሆነውን አይተውና ገምተው ከመደገፍ ይልቅ አፍራሽ ግብረሃይል ነው የሚያቋቁምብን። ሁልጊዜም አንድ ነገር ሲጀመር ከኋላ የመጎተት የመጠላለፍ ሙከራዎች ይደረጋሉ። ያንን ተወጥተን አብረን መቆም ከቻልን ውጤት ሊያመጣ የሚችል ብዙ ኃይሎችን ያሰባሰበ መደረክ ሆኖ መውጣት እንድሚችል እገምታለሁ።

ዘኢትዮጵያ- በምርጫው ዙሪያ ከኢህአዴግ ጋር በመደራደር በኩል እናንተን ከሌሎቹ የለያችሁ ምንድነው? ለምሳሌ ሌሎች እነ አቶ ኃይሉ ሻውል ከኢህአዴግ ሲደራደሩ እናንተ ከኢህአዴግ ጋር ለብቻችን ካልሆን አንደራደርም ብላችኋል ምክንያታችሁ ምንድነው?

ዶ/ር መረራ- እኛ አምስት መሠረታዊ ጉዳዮችን አንስተናል። ችግሩ ምንድነው መሰለህ። ለምሳሌ ሚዲያን ውስድ። ሚዲያን አፍኖ በሞኖፖል የያዘው ኢህአዴግ ነው። እነዚያ የፖለቲካ ድርጅቶች አይደሉም። እና ይህንን ሚዲያ የያዝከው አንተ ነህ የከለከልከን አንተ ነህ። ለምሳሌ ሰው የሚያሳድደው አባሎቻችንን የሚያስረው ኢህአዴግ ነው- እነዚያ ድርጅቶች አይደሉም። ስለዚህ አባሎቻችንን እያሳደድክ የምታስረው አንተ ነህ ማለት እንፈልጋለን። ቢሯችንን የምትዘጋው አንተነህ ልንለው እንፈልጋለን። ጉዳያችን ካንተ ጋር ነው። በምርጫ ስነምግባር በሚለው ከሌሎቹ ድርጅቶች ጋር ብንደራደር ችግር የለውም በእነዚህ በእነዚህ መሠረታዊና ወሳኝ ጉዳዮች ግን መደራደር እንፈልጋለን ነው ያልነው። ያፈንከን ያስርከን አንተ ነህና ካንተ ጋር መነጋገር አለብን ነው ያልነው።

ዘኢትዮጵያ- ለብቻችን ካልሆነ ያሰኛችሁ ምንድነው ሌሎቹ ድርድሩ ላይ ቢኖሩ ምን ጉዳት አለው?

ዶ/ር መረራ- ከልምድ የተረዳነው ነገር አለ። ከኢህአዴግ ጋር ብዙ ድርድሮች አድርገናል። ኢህአዴግ ጨዋታና ቲአትር ይወዳል። ኑ እንደራደር ብሎ ይሰበስብህና መጨረሻ ላይ መስጠት ሳይፈልግ ይኸው እነዚህ ድርጅቶች ተስማምተው ሲቀበሉ እነዚህኞቹ ግን አሻፈረኝ ብለው ረግጠው ወጡ ይልሃል። ይሄ አክራሪ ነው ይልሃል። ህብረት ላይ እንደዚህ ነው ያደረገን። አክራሪው ህብረት ነው እንጂ ያልተቀበለው ሌሎቹ ተቀብለዋል ብሎ ነበር።

ዘኢትዮጵያ- አሁንምኮ ታዲያ ከመባል አልዳናችሁም። ባትገቡም መድረኮች ረግጠው ወጡ አክራሪዎች ናችሁ እያላችሁ ነው

ዶ/ር መረራ- እሱ ሁሌም ዝም ተብሎ የሚወራ ስለሆነ ምንም ችግር የለውም። ግን እደራደራለሁ ብለህ ገብተህ አልቀበልም ብለህ መውጣት ምን ያደርግልሃል? ውጤት ያለው ሳይሆን የይስሙላ ድርድር ላይ ለምን ትቀምጣለህ? በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፖለቲካ ቲአትር ለምን ትሠራለህ? ኢህአዴግ ይህን ቲአትር ይፈልገዋል። እኛ ደግሞ የለም መሬት የያዘ ውጤ ያለው ድርድር እንፈልጋለን ባይነ ነን።

ዘኢትዮጵያ- ለምሳሌ እንዴት ያለ ነገር ላይ ነው መደራደር የምትፈልጉት?

ዶ/ር መረራ- ለምሳሌ ምርጫ አስፈጻሚዎች ጉዳይ መደራደር እንፈልጋለን። ይሄ ስነምግባር ምናንምን የሚባለው ነገር እሱ ችግር የለውም። ግን ወሳኝ ጉዳዮችን ከድርድር ውጪ እያደረግክ ነው። ይሄ ኮ ፈረንጆች ከጻፉ ኮፒ የተደረገ ነው። እዚህ ላይ ከተጻፉትም ህገመንግሥቱ ላይ ያሉ አሉ። ጉዳያችን እሱ አይደለም። ለምሳሌ ሰው ሳይታሰር ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ፣ ተቃዋሚዎች ቢሮ ከፍተው ያለምንም ወከባና መሰደድ ሊሠሩ ይችላሉ ወይ፣ ምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ ሆነው የህዝብ ድምጽ የሚቆጥሩበት አሰራር አለ ወይ? እነዚህን ነው ማንሳት የምንፈልገው። ኢህአዴግ ግን እነዚህን ዘሎ ሥነምግባር ላይ አንተ እንደዚህ አትስደበኝ እኔ አልሰድብህም፣ ይህን አታድርግ፣ ይህን አላደርግም… ወደሚለው ዝቅ ያደርገዋል። መሰረታዊ ነገሮችን ትቶ ወደስምነግባር ጨዋታ ያመጣዋል። ስነምግባር መሆን ያለበት ማሰሪያው ነው።

ዘኢትዮጵያ- እነ አቶ ኃይሉሻውል ለምን ከመድረኩ ጋር እንዳልተዋሃዱ የራሳቸውን ምክናያት ገልጸዋል። እንደሰሙት እገምታለሁ። የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ዶ/ር መረራ- እኔ እዚያ ውስጥ ባልገባ ደስ ይለኛል። እኔ እሳቸው ፖለቲካ አውቀው እንዲህ ይበሉ አይበሉ አላውቅም። ምን ትርፍ እናመጣለን ብለው እዚያም ውስጥ እንደገቡ አላውቅም። ለምን ብቻቸውን ተነጥለው እዚያው ውስጥ እንደገቡ እሳቸውን ብትጠይቁ ይሻላል። እነዚያ መሠረታዊ ጉዳዮች ሳይመለሱ ዋስትና ሳይሰጥ መግባታቸው ምክንያቱ አልገባኝም። እናውቀዋለንኮ። ከኢህአዴግ ጋር ብዙ ጊዜ ተደራድረናል፣ 101 ጊዜ ከድቶናል። ለማንኛውም ነገሩኮ ውሎ ሳያድር በሳምንትና ወራት ጊዜ ውስጥ ይታወቃል። ኢህአዴግኮ ካላሳረ ካላባረረ የኢትዮጵያን ህዝብ ማስተዳደር ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል። ይህን እሳቸውም ያውቃሉ እኛም እናውቃለን። እሳቸው እንደሚሉት ታሪካዊ ክንዋኔ ይሁን ሌላ ይሁን ወደፊት እናየዋለን። ፍቅራቸው እንደዚያ ይቀጥል ዳግመኛ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ቲአትር ለመስራት ይሁን በቀናት ውስጥ እናየዋለን። እኛኮ ኢህአዴግ እሳቸው እንደሚሉት ቢሆን ቢያደርግ ደስ ይለናል። ኢህዴግን የሚያውቁ የኢህአዴግ መሪዎች የነበሩኮ እኛጋ አሉ!

ዘኢትዮጵያ- እናንተ ምርጫው ላይ ትሳተፋላችሁ?

ዶ/ር መረራ- እሱን ዛሬ አንወስንም። ግን ለምርጫው እንሳተፋለን ብለን እንሰራለን። እየሠራንም ነው። እስከመጨረሻው ሠዓት እንሰራለን። የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚያስገባ ከሆነ እንገባለን፣ ካልሆነም ሁሉንም ጊዜው ይወስነዋል። እንጂ አሁን ምኑም ባልተያዘበት ሁኔታ እንገባለለን አንገባም አንልም።

ዘኢትዮጵያ- በምርጫው ለመሳተፍ ምቹ ሁኔታ ሊኖር ይችላል ብላችሁ አስባችኋል?

ዶ/ር መረራ- አሁን ባለው ሁኔታ የለም። የፖለቲካው ሜዳ እየጠበበ ነው።

ዘኢትዮያ- ለምርጫው የቀረው ጊዜ አጭር ነው። በዚህ ቀሪ ጊዜ ውስጥ ይሰፋል ብላችሁ ታስባላችሁ?

ዶ/ር መረራ- አዎ አንድም ቀን ቢሆን ይበቃል። አንዲት ቃልኮ ልትበቃ ትችላለች። ካድሬዎቻቸውን ሰው ማሰር አቁሙ ማለት በቂ ነው። ሚዲያው ነጻ ይሁን ማለት ነው። ፖለቲካ ድርጅቶች ቢሮ ከፍተው ይንቀሳቀሱ ተውአቸው ማለት ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ነገር አይደለም። ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎችን እንምረጥ ማለት ብዙ ጊዜ ሊፈጅ ይችል ይሆናል። የፖለቲካ ድርጅት አባላት ይፈቱ ማለት የአንድ ቀን ስራ ነው። እነዚህ እንኳ ብቻ ቢሟሉ ለምርጫ ለመሳተፍ በቂ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።

ዘኢትዮጵያ- የምርጫ አስፈጻሚዎችን ሥራ ከባድ የሚያደርገው ጊዜ የሚያስፈልገው ለምንድነው?

ዶ/ር መረራ- ወደ 200 ሺ የሚጠጉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ናቸው የሚሰማሩት። እነዚህ በሀቅ ገለልተኛ መሆናቸውን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል። እነሱን ለመመልመል እንኳ 200ሺ ሰው ብዙ ነው። ዋናው ጉዳይና ቁልፉ ደግሞ እሱ ነው።

ዘኢትዮጵያ- ወደ እርስዎ ድርጅት ወደ ኦህኮ ልምጣና የተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶች አሉ። ኢህ አዴግ ውስጥ ኦህዴድ አለ። ከውጭ ኦነግ አለ። እርስዎ ያሉበት መድረክም ውስጥ እስከማውቀው ሁለት የኦሮሞ ድርጅቶች አላችሁ። የእርስዎን ድርጅት ኦህኮን ከእነዚህና ከሌሎቹ የኦሮሞ ድርጅቶች ሁሉ የሚለየው ምንድነው?

ዶ/ር መረራ- እዚህ ላይ እንግዲህ ውጭ ያሉትን አቆይተን አገር ውስጥ ያለነው ለምሳሌ ከኦፊዴን ጋር መሠረታዊ ልዩነት እንደሌለን አረጋግጠናል። ስለዚህ ነው አብረን ለመስራትም የወሰነው። በመሠረታዊ የኦሮሞ ጥያቄዎች ላይ ልዩነት የለንም ከሚል ስምምነት ላይ ደርሰናል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮና ጥያቄዎችም ላይ ችግር የለንም። እኛ የኦሮሞ ህዝብ በሐቀኛ ፌደራሊዝም ችግሩ ይፈታል ብለን እናምናለን።

ዘኢትዮጵያ- ምንድነው ሐቀኝ ፌደራሊዝም ማለት?

ዶ/ር መረራ- አሁን ለምሳሌ ሥራ ላይ ያለው የይስሙላ ፌደራሊዝም ነው። ፌደራሊዝም የለም ብለን ነው የምናምነው እኛ። በወረቀት ላይ እንጂ በመሬት ላይ የሚታይ ፌደራሊዝም የለም። ለምሳሌ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ አይደለም። ከላይ በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ነው። ሰው ሲያስሩ፣ ሲገርፉ እናያለን። ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ የለም። የክልል ም/ቤቶች የተባሉት ኢህ አዴግ ያቋቋማቸው ናቸው። እንጂ የዚያ አካባቢ ህዝብ አምኖባቸው የተቀበላቸው አይደሉም። በመድረክ ውስጥ ያለነውንም በርካታ ድርጅቶች በጋራ ያሰባሰበን ይህ አቋም ጭምር ነው።

ዘኢትዮጵያ- በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የመድረኩም ሆነ የእርስዎ ድርጅት አቋም ምንድነው? እንደነ አቶ ኃይሉ ሻውል ያሉት ድርጅቶችም ይህንኑ በጥርጣሬ ሲያነሱ ይሰማሉ፣ አቋማችሁ ምንድነው?

ዶ/ር መረራ- የኢትዮጵያ አንድነት በግልጽ ቋንቋ ተቀምጧል። “በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ሥር የኢትዮጵያ ችግር ይፈታል” የሚል የማያሻማ አቋማችንን በግልጽ አስቀምጠናል። ኢህአዴግ የሚጠቀምበት ለምሳሌ የከፋፍለህ ግዛ ሤራ አንዱን ብሔረሰብ ከሌላው ጋር ማጋጨት ነው። የአገሪቱንም አንድነት በመጠበቅ ደረጃ ታማኝነት እንደሌለው ሲሰራ የነበረው ይታወቃል። ኢህአዴግ ከሥልጣኑ ውጭ ብዙ የሚያያቸው ነገሮች የሉም። ስለዚህ ስምንታችንም ድርጅቶች በሐቀኛ ፌደራሊዝም የኢትዮጵያ ችግር ይፈታል ብለን ተቀብለናል። ድሮ የኢትዮጵያን አንድነት እነ እንትና አይቀበሉም እነ እንትና ይቀበላሉ ይባላል። አንዳንዱ የኢትዮጵያዊነት ሠርቲፊኬት ሰጪ እኔነኝ ይላል። እኛ ግን እዚህ የተሰባሰብነው ኃይሎች የኢትዮጵያ አንድነት የተቀበልን ኃይሎች ነን።

ዘኢትዮጵያ- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች ሁሌ መገናኘት ሁሌ መለያየት ልማዳችሁ ነው። ለመሆኑ የአሁኑ የመድረክ አባላት ጥንካሬያችሁ ምን ያህል ነው? ይህ ላለመደገሙ ዋስትናችሁ ምንድነው?

ዶ/ር መረራ- እንግዲህ ፈተናውን ለነገ ብናደርገው ይሻላል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከልብ አብረን ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው።

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios