ፔንሰልቪኒያ የተባለው ግንቦት 7- ቤተመንግሥት ተገኘ?

(አስተያየት) ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ እየተወራ ባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተሳትፏል የተባለው የግንቦት 7 ንቅናቄ በአደባባይ ያንቀላፋውን ፖለቲካ እያነቃነቀው ይመስላል። ንቅናቄው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ላይ አለሁበትም የለሁበትምም ሳይል ሙያ በልብ ነው የሚል ይመስላል። የአራት ኪሎው ኢህአዴግም ሰኞ መፈንቅለ መንግሥት ነው ብሎ ማክሰኞ አፌን በቆረጠው የሚል ሆኖ ተገኝቷል። ሙከራው መንግሥት የመገልበጥ ሳይሆን ግድያና ሽብር የመፍጠር መሆኑንም በአቶ በረከት ሰምዖን በኩል እያስታወቀ ነው። ግንቦት 7ና ደጋፊው ወገን በበኩሉ አዘለም አቀፈም ያው ተሸከመ ነውና የተቃውሟችን ግቡ ህዝባዊውን የግንቦት 7 ድምጽ ገልብጦ ሥልጣን ላይ የተቀመጠውን መንግሥት መገልበጥ ነው እያለ ነው። አታስጎምዡን የሚለውም ጎራ ስሙ ሳይሆን ይልቁንስ ውጤትና እውነትነቱን አስረግጣችሁ ንገሩን ባይ መስሏል።

በአመጽ ደሴት ተከቦ የሚኖረው መንግሥትም ያገኘውን ሁሉ እያሳበበ እስር ቤት መስደዱ የሚጠበቅ መሆኑም የተገመተ ሆኗል። ለዚህም ይመስላል ከ40 በላይ ሰዎችን አስሬያለሁ ማለቱ ብዙም ያስደነቀ አይመስልም። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ፍጥረቱም አብዮታዊ ስለሆነ፣ አብዮት ልጆቿን መብላት ትወዳለች- የሚለውን ታሪክ ተመልሶ ሊሠራ ይመስላል። የኢህአዴግ አብዮት ልጆቿን እያበሰለች መሆኑ ያስታውቃል። አንዳንዱ ምግብ ቶሎ አይበስልምና እሳቱ ላይ ከተጣዱ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩት እነ አዲሱ ለገሠ፣ እነተፈራ ዋልዋ የበሰሉ ቀን መበላታቸው እንደማይቀር እየተወራ ነው። ከብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ንቅናቄ (ብአዴን) ወደ ግንቦት 7ቱ ንቅናቄ ተነቃንቀዋል የተባሉት አማራዎቹ የኢህአዴግ ልጆችም ተለይተው እየተለቀሙ መሆኑን በሪፖርተር ጋዜጣም ሆነ በሌላው በይፋ እየተነገረ ነው።

ከብአዴን አማራ ያልሆኑትና አማራነትን እንደጣምራ ብሄረሰብነት የተጠመቁት (ናቹራላይዝድ ያደረጉት) የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ አቶ በረከት ስመዖን ወልደ ገሪማ ብቻ ሲቀሩ፣ ዋና ዋናዎቹ ገበታ ላይ ሳይቀርቡ አይቀሩም እየተባለ ነው። የግንቦት 7ቱ ዋና ፀሐፊ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አባት ለምን ይታሰራሉ በሚል “እንዲህነችና!” ብለዋል የተባሉት የአቶ ተፈራ ዋልዋ ባለቤትም ታስረው መለቀቃቸውንም ሪፖርተር ጋዜጣ ጽፏል። የሚታሰሩ ሰዎች ምን ያህል ያሳስቧችኋል ተብለው በሰሞኑ የዋሽንግተኑ ስብሰባቸው ላይ የተጠየቁት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋም ይህ መሆኑ የሚጠበቅና አወቀንም የገባንበት ነው ብለዋል። እንዲያውም ግንቦት 7 ባርነት በቃኝ የሚባልበት የነጻነት ትግል በመሆኑ “ሁሉም ሰው ግንቦት 7 ነው!” አይነት አገላለጽ ተጠቅመዋል። ከዶ/ር ብርሃኑም ተደጋጋሚ ማብራሪያዎች መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር ከታሰሩ ሰዎች ውስጥ የግንቦት 7 የንቅናቄ አካል የሆኑ ሰዎች አሉ። ከመንግሥት መግለጫ፣ ከሚጠበቅ ባህሪውና ከታሪኩ አንጻር ደግሞ፣ የታሰሩት ሁሉ የንቅናቄው አባል አለመሆናቸውን በቀላሉ መገመት ይቻላል። ህገ መንግሥቱን በኃይል ለመገልበጥ ሲል- ሆስፒታል ተኝቶ የነበረን አስክሬን በመኪና ገጭቶ ገድሏል- ሳይባል አይቀርም የሚባለው የቴዲ አፍሮም ነገር አይረሳም። ኢህአዴግ በገደለው ለምን ይቅርታ አልጠየቅሽም ተብላ እስር ቤት የተጣለችው ወጣቷ የልጅ እናት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ አገሪቷን ከማይታመን መንግሥት ሥር ጥሏል።በመሆኑም የተነገረውን ሁሉ ለማመን አስቸጋሪ ማድረጉ አልቀረም።

በሌላም በኩል ጉዳዮን ከዘረኝነት እርምጃ ጋር አያይዞ የሚሰራጨው የግንቦት 7ቱ መግለጫም መንግሥት የተነጠሉትን ደጋፊዎቹን ለማሰባሰብ ሰበብ እንዳይሆንለት ማስጋቱ ግልጽ ነው። ኢህአዴግና ደጋፊ ልሳናቱ መንግሥት እንደዚያ ማድረጉን መግለጻቸው ግልጽ ስለሆነ ያንን ደግሞ የማስተጋባቱ ነገር የመንግሥትን ፍላጎት ከመደገፍ የተለየ ውጤት ያለው አይመስልም። በሌላም በኩል ከማንም ያልተናነሰ ጭቆና ሥር ያሉትንና በስምና በማንነታቸው ተደምረው ከሥርዓቱ ጋር የሚወቀጡትን ወገኖች እንዳያሳዝንና ትግላቸውንም ከሁለት ቤት እንዳይሆን የማድረጉ አስፈላጊነት ብዙ ያስጨነቀውም አይመስልም። “ጥቂት ዘረኞች” የሚለው አገላለጽ ጥቂቶችን ብቻ ለይቶ የሚመታ አገላለጽ አለመሆኑ ሲታይ የኖረ ነው። “ጥቂት” የምትለዋ ቃል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዝነኛ እንጂ የዋህ ቃል አይደለቸም። “ዘር” የሚለውም ቃል ብዙ ርቆ የሚያስኬድ ነገር አይደለም። ጥንቃቄ ኖረም አልኖረም ጎሰኝነት ያደረበት ሁሉ ከዚያ አባዜ ሊላቀቅ አይችልም፣ ወይም አካፋን አካፋ ማለት ተገቢ ነው፣ ወይም ያበጠው ይፈንዳ ! የሚል አካሄድ ምርር ባለቁጥር ትዝ የሚል ስሜት ቢሆንም ጥሩ ስትራቴጂ አይደለም። በተለይ አቶ መለስና አገዛዛቸው በተነካ ቁጥር የትግራይ ህዝብ እንደተነካ አድርገው ማቅረብ ለሚፈልጉና በዚያም አንጻር ብቻ ተነጂዎችን ለሚነዱ አውቆ አጥፊዎች ሌላ የቂምና የጭካኔ ዱላ ማቀበል እንዳይሆን የሚያስብ ኃይል አስፈላጊነት አሁንም እንዳለ ነው። እነ ስዬ አብርሃ ነገ ከግንቦት 7 ጋር ተደምረው እንደገና ቢታሰሩም አንድናቸው፣ አውቀው ሊሰልሉንና ሊያታልሉን ነው! ማለት ሌላው ጭካኔና ከዚያኛውም ያልተለየ ጎሰኝነት ነው። ጎሰኝነት በጎሰኝነት አይጠፋም። ትግሉን ውስብስብና አስቸጋሪ አድርጎ ያቆየውም ይህ ኑግና ሰሊጥ ያልተለየበት ሜዳ መኖሩ እንጂ ወያኔዎቹ እንደሚያላዝኑት የወንድነትና የቆራጥነት ነገር አይደለም። ለማንኛውም የግንቦት 7 መግለጫን መጥቀሱ ደህና ሳይሆን አይቀርምና የመግለጫው መደምደሚያ እንዲህ ይላል፤-

ከቁጥጥር ውጭ በመውጣት ላይ የሚገኝን፣ መለስ ዜናዊና ጥቂት ዘረኞች ህዝብን በዘር እየለዩ የሚወስዱትን የማጥቃት እርምጃ፣ ይህ ድርጊት ለዘመናት አብሮ በኖረ ህዝብ መካከል ጥሎ የሚያልፈውን ቂም የምትገነዘቡ በዘረኛነት ያልተለከፋችሁ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የወያኔ ፖለቲካ ድርጅት አባላት እንዲሁም ሌሎች የትግራይ ልጆች ይህን የዘር ማጥራት ተግባር በግልጽና በአደባባይ እንዲኮንኑ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ጥቂት የወያኔ ባለስልጣናት በወያኔ አባላት ስም በጦር ወንጀልና በዘር ማጥፋት የሚያስጠይቅ ዘግኛኝ ወንጀል እየፈጸሙ፣ አሁንም በእዚሁ የጥፋት ጎዳና ሲነጉዱ ‹‹ በእኛ ስም አይደረግም›› የሚል ተቃውሞን አለማሰማት በዝምታ በተደረገ የተባበሪነት ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ወቅቱ ሳይረፍድ ልናስታውሳቸው እንወዳለን፡፡

ይህ የግንቦት 7 ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ፣ የትግል አጋርነትን የሚጋብዝ ጥሪ ሆኖ፣ በወያኔ ሓርነት ትግራይ ደጋፊዎች ስለመወሰዱ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ሁሌም እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ነገር ቢኖር፣ “ይህን መንግሥት የነካ እኛን የነካ ነው!” የሚል የህብረተሰብ ክፍል የመኖሩን ሐቅ ነው። ይህ የህብረተሰብ ክፍል ጥቂት የሚባል ባይሆንም ሕዝብ ተብሎ የሚጠራ እንኳ ቢሆን “ሰፊው ሕዝብ” የሚባል “ሕዝብ” አለመሆኑምም ደግሞ ስለመረረና ስለጣፈጠ የሚክዱት ሐቅ አይደለም። እነዚህን ሁለት ሐቆች አስታርቆ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ሰለማዊ የአንድነት ጎዳና ይዞ የሚጓዝ ጠንካራ አካል ማስፈለጉ ነገር ከመበላሸቱ በፊት ፈጥነው የሚናፍቁት ነገር ነው።

ከጠመንጃ በላይ ፍልስፍናቸው የሚያምርባቸው እነዶ/ር ብርሃኑ ነጋም በሰላማዊው ምርጫም ሆነ በለሌኛው መንገድ የት ድረስ መሄድ እንደሚችሉ ለተቃራኒዎቻቸውም ሆነ ወዳጆቻቸው አበክረው ማሳየታቸው የሚካድ አልሆነም። የግንቦት 7ቱ ንቅናቄ ከፒንሲልቪኒያ ጫካ ውስጥ ያለ ነው እንዳልተባለው ሁሉ አራት ኪሎን ማስጨነቁን የተጨነቀው እየነገረን ነው።

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios