መንግሥት በጥላሁን ገሠ ሠ እረፍት መግለጫ አወጣ

ታላቁ የዘመናችን የስነ ጥበብ ሰው አርቲስት ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ዜና እረፍት በማስመልከት መግለጫ ማውጣቱን የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚከተለውን መግለጫ ማውጣቱ ተዘግቧል።

የዘመናችን ታላቁ የስነ-ጥበብ ሰው የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሞት መላውን ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ሀዘን እንዲዋጡ አድርጓል፡፡

አርቲስት ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በቆየ ታላቅ ህዝባዊ አገልግሎቱ የመላውን ኢትዮጵያውያን መንፈስ ሲያድስ የኖረ ምርጥ የስነ-ጥበብ ሰው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ከሱ በኋላ ለተፈጠሩ የስነ-ጥበብ ሰዎችም ታላቅ አብነት በመሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ምርጥ አርቲስቶችን ያፈራ ፈር ቀዳጅ የስነ-ጥበብ ሰው ነበር ፡፡ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በዘፈኖቹ ያልዳሰሰውና ወደር በሌለው ቅላፄው ያላንጎራጎረበት የህይወት ገፅታ አልነበረም፡፡ ስለ ፍቅር፣ ስለደስታ፣ ስለሀዘን፣ ስለችግርና ሰቆቃ፣ ስለመተሳሰብና መቻቻል እንዲሁም ስለአገርና ሕዝብ ያቀረባቸው ዘፈኖቹ የኢትዮጵያውያን የመንፈስ ምግብ ሆነው ኖረዋል፡፡ በተለይም በ1966 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅ በችግሩ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ ያቀረበው ዜማ ምንጊዜም የሚታወስ ነው። ዕውቁ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ለመጨረሻ ጊዜ በሕዝብ መድረክ ላይ ቀርቦ የታየው አገራችን ኢትዮጵያ አዲሱን ሚሌኒየም በተቀበለችበት ወቅት ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ ባዜመበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል። ይህም ታላቁ የዘመናችን ምርጥ አርቲስት ያልጋ ቁራኛም ሆኖ እያለ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የነበረውን አክብሮትና መልካም ምኞት ለመግለፅ ምንም ነገር የማያግደው እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ታላቅና ዕውቅ አርቲስት በሁሉም የአገራችን ህዝቦች እንዲወደድ፣ እንዲከበርና እንዲደነቅ ባደረገ ሕያው ስራው ሁልጊዜም የሚታወስ ይሆናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግሥት ለቤተሰቦቹ፣ ለአድናቂዎቹና ለመላው የሀገሪቱ ህዝብ ልባዊ መፅናናትን ይመኛል፡፡

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios