ቴድሮስ አድኻኖም ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ?

አቶ መለስ ዜናዊ የፓርቲው ሊቀመንበር?

አቶ መለስ ዜናዊ በሊቀመንበርነት የሚመሩት የወያኔ ሓርነት ትግራይ ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት 45 ናቸው። ከአንድ ሰው በስተቀር ሁሉም በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ጀምሮ በረሃ እያሉ ይተዋወቃሉ። አቶ መለስን ጨምሮ አንዳንዶቹ እንዲያውም ባልና ሚስት እህትና ወንድም ጋብቾች ወይም አብሮ አደጎች ናቸው። በእድሜም በአስተሳሰብም በቁመናም ሳይቀር ከእነሱ ለየት ያሉትና ምናልባትም እነሱ በረሃ በነበሩ ጊዜ አስመራ ትምህርት ቤት የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም ብቻ “ከውጭ” የመጡ ሰው ናቸው። አቶ መለስ የሚወዷቸውና ትኩስ ኃይል ናቸው የሚሏቸውን እኚህን ሰው ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር “አስመስለው” ያስቀምጧቸዋል የሚል ነገር እየተሰማ ነው።

በሚቀጥለው ምርጫ ሥልጣናቸውን ሊለቁ እንደሚችሉ እየደጋገሙና ፈራ ተባ እያሉ የገለጹት አቶ መለስ ዜናዊ ቃላቸውን የሚያሳዩበት ጊዜ እየደረሰ ይመስላል። ነገ ዓርብ ኤፕሪል.10 በሚደረገው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባም ጉዳዩን ያነሱታል የሚል ወሬም ተሰምቷል። አቶመለስ አንዴ በቅቶኛል ሌላ ጊዜ ደግሞ ፓርቲዬ እንደ ፈቀደ አደርጋለሁ እያሉ መክረማቸው የሚታወቅ ቢሆንም እስካሁን ቢያንስ በሶስት የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ተጠይቀዋል። አንዴ ከራሳቸው አፍ ያመለጠ ነገር ነውና በየሄዱበት መጠየቃቸው ምቾት ሳይነሳቸው አልቀረም።

ያም ብቻ ሳይሆን ባለፈው ጊዜ የተሸነፉበት ምርጫ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ጥሎት የሄደው ጠባሳ አሁንም ቢሆንም ፈጦ መታየቱ አልቀረም። በአፍሪካ ፖለቲካ የአንድ ሰው ሥልጣን የአገር ሥልጣን ተደርጎ ስለሚታሰብ የሳቸው ከሥፍራው ዞር ብሎ መታየት በኢትዮጵያ ለውጥ እንደመጣ ተደረጎ የሚወራበት አጋጣሚ ትልቅ መሆኑም አይካድም። ካድሬዎቻቸውና ወዳጆቻቸውም ይህ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ ታሪካዊ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ነው ብለው ማዳነቃቸው አይቀርም። በዚህኛው ከበሮ ይበልጥ ደምቀው የሚወጡት አቶ መለስ ዜናዊ በፓርቲው ውስጥ ሆነው መንግሥታቸውን ያለሀሳብ እያስተዳደሩ ለመቀጠል እንደሚያስችላቸውም ይታመናል።

በሌላ በኩልም እሳቸውን ይተካሉ ከተባሉት የኢህአዴግ ሰዎች አቶ ግርማ ብሩና አቶ ቴድሮስ አድሓኖም እንደታሰቡ ሹክሹክታ መኖሩን ፎርቹን ባለፈው ሳምንት ጽፏል። ይሁን እንጂ የአቶ ግርማን እንኳ ብዙም ያልተዋጠለት ወይም እንዲዋጥልን አድርጎ አለመለጻፉ ያስታውቃል። የሆኖ ሆኖ የቴድሮስ አድሓኖም ጉዳይ ቀደም ሲል ጀምሮ የታሰበበትና ወደፓርቲው ከፍተኛ ሥልጣን እንዲመጡ ሲደረግም ዝግጅት መኖሩን ውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ። ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሲሆን የወያኔ ሓርነት ትግራይ ሥራ አስፈጻሚ አባል (ፖሊት ቢሮ አባል) ናቸው። በፓርቲው ታሪክ በትጥቅ ትግሉ ሳይሳተፉ ወይም በረሃ ሳይወርዱ ወደ ፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ እንዲገቡ የተደረጉ እሳቸው ብቻ መሆናቸው ይነገራል። ቴዎድሮስ አድኻኖም ገብረየሱስ በ1986 ከአስመራ ዩኒቨስቲ በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ሲገለጽ በተለያዩ የጤና ትምህርቶች ከሁለት የእንግሊዝ ዩኒቨስርቲዎች ከፍተኛ ዲግሪዎቻቸውን ማግኘታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ኢህአዴግ ከተሸነፈበት የምርጫ 97 በኋላ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው እስኪሾሙ ድረስ ሚኒስቴሩን በረዳትነት ሲመሩ ቆይተዋል።

ካሁን በኋላ በየሳምንቱ እየወጣሁ ስለ መንግሥትን እንቅስቃሴ መግለጫ እሰጣለሁ ብለው የተነሱት አቶ በረከት ስምዖን ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያውን መግለጫ ሰጥተዋል። (እንደ ዋይትሐውስ ዴይሊ ብሪፊንግ መሆኑ ነው) በመግለጫቸው ኢህአዴግ በሚቀጥለው ምርጫ ጉዳይ ለመነጋገርና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋርም ስለምርጫው ለመመካከር ማሰቡን ገልጸዋል። ስማቸው የፈለገውን ቢሆንም የመንግሥት ቃላ አቀባይ ሚኒስትር የሆኑት የአቶ በረከት መግለጫ ያወራ የነበረው ስለፓርቲ እንጂ ስለመንግሥት አልነበረም። በኛ አገር መንግሥትና ፓርቲ አንድ ናቸው ካላሉን በስተቀር ማለት ነው። እሱም ቢሆን ግን ኢህአዴግ ስለሚቀጥለው ምርጫ አጠቃላይ ሁኔታ ለመምከር ስበሰባ መቀመጡን መግለጻቸው ስለሆነ የሚጠላ ኢንፎርሜሽን አይደለም። ክእሳቸው መግለጫ ቢያንስ ሁለት ነገር መረዳት ይችላል። አንደኛው ኢህአዴግ በሚቀጥለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አለ ብሎ ማሰቡን ብቻ ሳይሆን ለዚህም ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ አለብኝ ብሎ ተነስቷል። ይህ መሆኑ ሌላውን እንኳ ባይችል ቢያንስ ራሱን ደግሞ ለማሞኘት መዘጋጀቱን ያሳያል ማለት ነው። ሁለተኛ ተቃዋሚዎችንና ተቃውሞን በማፈን ከሚያካሂደው ምርጫ በአሸናፊነት ለመውጣት ጥሩ ማምለጫ ዘዴ አድርጎ የወጠነው የአቶ መለስ ዜናዊን ከሥልጣን መነሳትና በሌላ ሰው መተካት ነው። ይህ የሚፈጥረው ዜና ሌላውን አጀንዳ በማስቀይርም ሆነ በማዘናጋት የሚፈጥረው ሚና ከፍተኛ ስለሚሆን ኢህአዴግ ከዚህ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን መካድ አይቻልም። “አንዳንድ መጠነኛ ችግሮች ቢኖሩበትም የ2005ን ምርጫ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ነበር” ብለው መግለጫ የሰጡት ዓለም አቀፍ ተቋማትም “ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊና ታሪካዊ የሥልጣን ሽግግር አደረገች!” ብለው ፈጥነው ከማወደስ አይመለሱም።

የፓርቲውን ንብረት በሙሉ እንዲቆጣጠሩ የኤፈርት ም/ሊቀመበር ሆነው በፓርቲው ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ ሰሞኑን የተሾሙት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጉዳይ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚችል መሆኑም ይታያል። ከወ/ሮ አዜብ በላይ ለአቶ መለስ የሚቀርብ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ከሥልጣን “ወርደው” የፓርቲው ሊቀመንበር ለሚሆኑት አቶ መለስ ዜናዊም አገር የሚገዛ ፓርቲቸውን ያለምንም ሀሳብ ከመኝታ ቤታቸው ሆነው ሊመሩት ይችላሉ ማለት ነው። አቶ መለስ እየቀረበላቸው ካለው ማስተባበያ አንደኛው- አሁንስ ደከማቸው 38 ዓመት ሙሉ ያለ እረፍት ቀን ከሌሊት ስለሰሩ አሁን እረፍት ያስፈልጋቸዋል- የሚል ነው። በተጠዳደፈ ሁኔታ ውስጥ እንዲህ ያለ የሥልጣን መረብ መዘርጋት የቻሉት አቶ መለስ ዜናዊ ከውጣ ውረዱ ሁሉ አረፍ በሚሉበት ጊዜ ደግሞ ምን ሊሠሩ እንደሚችሉ መገመት አይቸግርም። ምእራባውያን ይወዷቸዋል የሚባሉት፣ ለስላሳው፣ ሽቁጥቁጡ ግን ደግሞ ጠንካራና ታታሪ ሠራተኛ የሆኑት የአስመራው ቀልጣፋ፣ አቶ ቴዎድሮስ አድኻኖም ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ የተሻለ መልክ በቴለቪዥን ከማየት ውጪ ሌላ ነገር ሊኖረው ሰለመቻሉ ክወዲሁ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም።

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios