ይልቅ ወሬ ልንግረህ!

ሩፋኤል ውበቱ
ወይ ቤተመንግሥቱን ወይ ልመናውን ተውልን!
ልመና በህግ እንዲከለከል በፓርላማ ተጠየቀ

አንድ የአዲስ አበባ ለማኝ፣ ጓደኛው ከሆነውና አብሮት ተቀምጦ ከሚለምነው የሌላ ክልል ቋንቋ ተናጋሪ ጋር እንደ አቅሚቲ ሁሌም ፖለቲካ ያወራሉ። ዘመኑ ራሱ ባመጣው የጎሳ ጨዋታ ምኑም ውስጥ የሌሉበት የኔቢጤዎች እንኳ ሳይቀሩ አንዳንዴ እኔነኝ የምገዛህ የለም ንጉሥህስ እኔነኝ እየተባባሉ ይቀላለዳሉ። ተካፍሎ መብላቱንና መተሳሰቡን ባያስቀርባቸውም አልፎ አልፎ ቀልዱ መረር ማለቱ አይቀርም። አንድ ቀን አንደኛው ለማኝ እንደለመደው እኛኮ አገሩን በሙሉ ተቆጣጥረነዋል እያለ ይመጻደቃል።ያኛው ለማኝ ቀበል አድርጎ “ታዲያ ወይ ቤተመንግሥቱን ወይም ልመናውን ተውልን እንጂ ! እንዴት ነው አንተና ዘመዶችህኮ እዚህ ከኛው ጋር ስታጋፉ እያየናችሁ ነው። ሁሉንም ነገር ካልያዛችሁት አትወዱም ማለት ነው…” ሲል መቀለዱ አዲስ አበባ ሲቀለድበት የኖረ ነው። የዛሬውን የሪፖርተር ጋዜጣ ዜና ቢሰማ ይኸኛው የኔቢጤ ለማኝ ምን ሊል እንደሚችል መገመት ይቻላል። ልመናን በህግ የሚከለክል ህግ እንዲወጣ አንድ የፓርላማ አባል መጠየቃቸውንና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩም ሀሳቡ በሁለተኛ አማራጭነት የሚያዝና የሚደገፍ መሆኑን መናገራቸው ተዘግቧል። ኢኮኖሚውን በልመና እርዳታ የሚያሳድገው፤በጀቱን እንኳ ሳይቀር በልመና የሚያገኘው መንግሥት፤ ራሱ ለማኝ ሆኖ ማብላት ማጠጣት እያቃተው፣ በሌላ በኩል እንዲህ ያለ ሀሳብ ማምጣቱ ይገርማል። አቶ መለስ እኮ በምርጥ ለማኝነታቸው፣ እንኳን ለኢትዮጵያ ለአፍሪካ መለመን ይችላሉ፣ ተብለው በቡድን 20 (G20) ስብሰባ ላይ እንዲካፈሉ የተጋበዙትና እያስፈራሩ የለመኑት ሰሞኑን ነበር። ለነገሩ ተበዳሪያችን 43ኛው ቢሊየነር ሼህ አል አሙዲ ሰሞኑን በሰጡት የሬዲዮ ቃለ መጠይቅ፣ “በቅርቡ ከሳውዲ አረቢያ ከሚመጡት” በርካታ የአረብ ኢንቨስተሮች ጋር ሆነን ግብርናው ላይ በመሰማራት አገሪቱን ሙሉ ሙሉ ከረሀብ ነጻ ባናወጣት መሀመድ ምን አለ በሉኝ… ማለታቸውን ሰምተናል። ለማኞችን በማብዛት ሳይሆን “በመቀነስ” የሚታወቁት ሼኽ መሀመድ ፣ ኢትዮጵያችንን ህይወታቸውን እስከመስጠት ከሚወዱት መንግሥታቸው ጋር ሆነው፣ የጥጋብ አገር ሲያደርጉ ልመና ራሱ ይጠፋልና ቢታገሱልን ጥሩ ነበር። ወይም ኢኮኖሚስቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ እንዲበላ እናደርገዋለን የሚለውና ዘመን ያስቆጠረው እቅዳቸው እንዲሳካ ቢያደርጉ ለማኙ ሳይሆን ልመናው ራሱ ጥርግ ብሎ ይጠፋል። ድህነትን ከማጥፋት ድሆችን ማጥፋት የሚለውን ክርክር እንደገና ልንጨዋወት ነው። ለማንኛውም በቀን ሶስት ጊዜ እንዲበሉ እየተመረጡ የተባረሩ ለማኞች እንኳ ሳይቀሩ ተመልሰው ልመና እየገቡ ማስቸገራቸውን ሚኒስትሩ ፓርላማ ላይ አምነዋል። ሚኒስትሩ እንደሚሉት “አንዳንዶቹ ሰዎች ወደ ልመና የሚገቡት ስራ ጠፍቶ ሳይሆን ልመና ብዙ ሳይደከምበት ገንዘብ የሚያስገኝ ቢዝነስ ሆኖ ስላገኙት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሀሳቡን ያቀረቡት የአንድ ተቃዋሚ ድርጅት ተወካይ ናቸው። መንግሥትም ሀሳቡን አልጠላውም። ሲመጣበት ለማኞችን ራሱ እያፈሰና እያፈናቀለ የሚወስደውን መንግሥት ለማበረታት ድርጊቱን በህግና በአዋጅ እንዲያደርገው የሚመክረውን ተቃዋሚ ለምን ብሎ ይቃወማል? ይልቅ የሪፖርተሩ ዜና ያውላችሁ።

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios