የገንዘብ ሚኒስትራችን እድሜ ስንት ነው?

ሰሞኑን መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር በውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ መንግሥት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ነው ማለታቸው ተዘግቧል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተፈጠረው የዓለም የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት የነዳጅ የሸቀጦችና የኮንስትራክሽን እቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ገልጸዋል። በውጭ ምንዛሪ የሚጠቀሙ ነጋዴዎችም ሆኑ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በመመካከር፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ጥራት በመጨመርና በብዛት በመላክ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ማሻሻል እንደሚኖርባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የነዳጅና የማዳበሪያ ዋጋ መሻሻል ማሳየቱንና በቀጣይም የበለጠ ይሻሻላል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለፁት ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ሰዓት ትልቁና ፈታኙ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር መሆኑን መናገራቸውንም ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተከሰተበትን ምክንያት በተመለከተ አንዳንድ ሰዎች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ገንዘብ በመቀነሱ አድርገው የሚገምቱ እንዳሉ የገለፁት አቶ ሱፊያን፣ “በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርሻ ከዓመታዊ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አንድ በመቶ ብቻ ነው፡፡ እስካሁን (8ኛው ወር ድረስ) የሚላከው አልቀነሰም፡፡ እስከ በጀት ዓመቱ ድረስም ይቀንሳል የሚል እምነት የለኝም” ካሉ በኋላ፤ ከኬንያ፣ ከቦትስዋናና ከዩጋንዳ ጋር ሲነፃፀር ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው በጣም ትንሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

“የውጭ ምንዛሪ ችግር በእድሜዬም ይፈታል ብዬ አስቤም አላውቅም፡፡ ከእኛ ጋር ይቀጥላል” ካሉ በኋላ ምርት በማሳደግ ቀውሱ እንዳይሳፋፋ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው የተገኘውን በቁጠባ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አቶ ሱፊያን መክረዋል፡፡ በአንድ በኩል ዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብቷል በሚባልበት በዚህ ወቅት እንኳ የኢትዮጵያ ኢክኖሚ በፍጥነት እያደገ ነው ይባላል። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከኢኮኖሚ ጋር ተያያዥነት የለውም ካልተባለ በቀር በ እድሜዬ ይፈታል ብዬ አስቤ አላውቅም ከኛ ጋር ይቀጥላል ከሚሉት ሚኒስትር አባባል ማንሳት የሚቻለው ጥያቄ ቢኖር የሚኒስትሩ እድሜ ስንት ነው ማለት ብቻ ይሆናል። እሳቸው ሥልጣን ላይ ብቻ ሳይሆን በ ህይወት እስካሉ ድረስ የማይወገድ ችግር ከሆነ ችግሩን የሚወገድበትን ዘመን እንኳ ለማስላት መነሻ ጊዜ ያስፈልገናል ማለት ነው።

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios