ከመንጋው ፈቀቅ በል!

ጊዜው አጭር ነው። አምባገነኖች አይሻሻሉም፣ ጠማሞች አይሰተካከሉም። ደናቁርት አይጠበቡም። ስግብግቦች አይጠግቡም፣ ሌቦች አይታቀቡም፣ ፖለቲከኞቻችን አንድ አይሆኑም..ነጻ ወጪዎቹ ጎሰኞች ነጻ ወጥተው አያበቁም! ተገዢም ሆነው ገዢም ሆነው አየናቸው። የበታችነትና የጥላቻ ስሜትን ከደማቸው ውስጥ ለማጠብ የህይወት ዘመናችን አይበቃም። በዚያ ላይ በዚህች አጭር እድሜ በአጭሩ የሚቀጭ ችግር የለንም። ለውጥ ገና ናት። ተወደደም ተጠላም እውነቱ ይህን ይመስላል። ተስፋ ለማድረግ ተስፋ መቁረጥ ሳያፈልግ አይቀርም። ወይንም ተስፋ መለወጥ!

እስኪ ተመልከቱት፣ ችግራችን ብዙ ተስፋችንም የሱን ያህል ነው።
ነገራችን ሁሉ “ዳቦ የለም እንጂ ማርሜላት ቢኖር ኖሮ እንዴት ርቦኝ ነበር እንዳለው ሰውዬ” መሰሏል። ዳቦውም የለም ማርሜላቱም የለም። ንግግር ሲያሳምሩ የሚደመጡ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን የሚያሞግሱት የእጦቱን ብዛት ከደረደሩ በኋላ ነው። አንድነት የለንም እንጂ መፈቃቀር ቢኖር ኖሮ፣ የረባ ተቃዋሚ ድርጅት የለም እንጂ፣ እንደወያኔ ዓይነት አሳፋሪ መንግሥት ባይኖር ኖሮ፣ አገሪቱ ደግሞ በኢኮኖሚ አድጋ ቢሆን፣ ይሄ በሽታ ረሀብና ጦርነት ባያጠቃን …አገራችን ኢትዮጵያኮ ከማንም የማታንስ አገር ነበረች! ይህ የትም የሚሰማ አባባልና አገላለጽ ይመስላል። እንዲህ ከተገለጸ በኋላም፣ በአንድ ቃል፣ በአንድ መድረክ፣ በአንድ ሰው፣ የኢትዮጵያ ችግር መፍትሄው እኔ ዘንድ ይገኛል፣ ቃሉም ያውላችሁ፣ ማድረግ የሚገባን እንደዚህ ነው ሲባል ይሰማል። ከገበታ ጠረጴዛ ውይይት አንስቶ እስከ ተንቦረቀቀው አዳራሽ ድረስ የዚህ ድፍረት ያለን ብዙ ነን። አስፈሪው ድፍረታችንም ለገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካዊ አመራር ሰጪነት ባለን ስግብግብነት እየተገለጸ ይመስላል።

ስግብግብነት በብዙዎቻችን ዘንድ ሆነ። ፕሬዚዳንትነና ሊቀመንበርነቱ ቀርቶ በግል እንኳ ለአኗኗራችን የምንፈልገው ትልቅ ነው። ገንዘብን በትልቁ እንፈልጋለን። ለማለም ያህል እንኳ ትንሹ እሺ አይለንም። በሺዎች ሳይሆን በሚሊዮኖች ነው። እሱንም የምንፈልገው በአቋራጭ ነው። ለመስራት ጊዜ የለንም። መንግሥትም እንዲሁ ቶሎ ግልብጥ እንዲልልን እንፈልጋለን ለትግል ግን ጊዜና ትእግስቱ የለንም። ትእግስት ከማጣታችንም አልፎ ታግሎ ታግሎ እንደታከተው ሰው ተስፋ ቁርጥ አድርገን ቅልብስ ምልስ እንላለን። በዚህ የተነሳ የምንጠላውን አካል “መንግሥቴ ነህ” ብለን በህዝብነት ልናድርለት ብድግ ብለን ወደ ኢትዮጵያ የምኖርጥ በዝተናል። ፖለቲካ “አንወድም” ወይንም “በቃን” ያልነውም ኑሮ ለመጀመር ተነስተናል። ።ግን ወዴት እየሄድን ነው?

ኢትዮጵያ ጸጥ ባለ ውሃና ጫካ እንደተከበበች ደሴት የምትመስለን ሁሉ መኖሪያችንን እየገነባን ዓለማችንን ልንቀጭባት እናልማለን። አሁን አሜሪካ ትንሽ ነገር ሠራ ሠራ አድርገን አገራችን እንገባለን። ቤታችን ካለቀ፣ ኢትዮጵያ እፎይ የምንልባት አገር ናት። ትልቁ ቤታችንን አከራይተን ትንሿን ቤት ተከራይተን እንኖራለን። እኛን ችሎ የሚቀጥር ሥራ አይገኝም እንጂ ቢገኝም አንሠራም። ኢትዮጵያ ማረፊያችን ናት! ….አሮጊቷ ላይ ተኝቶ ለመንደላቀቅ እንጂ እሷን ካለችበት የማላቀቅ ሞራል የጠፋ ይመስላል። ይህስ ባልከፋ ግን ያንን የምንፈልግበት መንገድ የከፋና የከረፋ ነው። ያባትህ ቤት ሲዘርፍ አብረህ ዝረፍ ታውጇል። ኢትዮጵያም “ሻሞ!” የተባለች መስላለች።

አገር ዘራፊዎችን ብንወቅስም እኛም ውስጣችን በማስተባበያ ተወሯል። ለውጥ እየታየ ነው፣ አዲስ አበባም እያደገች ነው… በሚል መግቢያ የሚንደረደረው ውስጣዊ ሕልማችን ሲፈታ እንደሚከተለው ይዘረዘራል፦ በቀረችው ዘመናችን በተድላና በደስታ እንኖራለን። ይህ መንግሥት ቢወገድ ጥሩ ነው። ካልሆነም ግድ የለም ፖለቲካ ውስጥ ካልተገባ መኖር እንችላለን። የተራቡትን አለማየት ነው። አቧራ የሚያገሱትን አለማስተዋል ነው። ሜዳ የተበተኑት መንገድ አዳሪ ወላጅ አልባ ህጻናት ድሮም ነበሩ፣ አሁንም አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ፣ ምን አዲስ ነገር አለ?! ይህ ሁሉ በእኛ ጥፋት የሆነ ነገር አይደለም፤ በኛ አቅም የሚወገድም አይደለም። ደግሞ ድህነት በዓለም የመጣ ነው። የኢኮኖሚ ውድቀት የትም አገር ያለ ነው። አልጠገብ ባይነት የትም አገር አለ። የባላሥልጣናት ብልግና ቅሌትና ውንብድና በሠለጠኑት አገራት እንኳ አለ። ኢትዮጵያ ጭካኔን በሞኖፖል አልያዘችም። መአትም በኢትዮጵያ ብቻ አልወረደም። በዓለም የመጣ ነው። እግዜር ያመጣውን እሱ ይመልሰው እንጂ ምን ይደረጋል? የእኛ ኃላፊነት ዝም ብሎ መኖር ነው። መኖር ካልቀረ ደግሞ ደህና ኑሮ መኖር ያስፈልጋል። ለነገሩ ደህና ኑሮ እኮ ማለት ምቾትና ቅንጦት የሚባለው ነገር አይደለም። ዛሬ እሱ የግዴታ ያህል የሚያስፈልግ ተራ ነገር ሆኗል።

በዚያ ላይ ህዝቡ፣ ማህበረሰቡ፣ ህብረተሰቡ፣ ኮሙዪኒቲው፣ ማንትስና ምንትሱ እያሉ ማሰብ ከሶሻሊዝምና ኮሙዩኒዝም ጋር ቀርቷል። ዘመኑ የካፒታሊዝም ነው። አሁን ነገር ሁሉ የተገላቢጦሽ ነው። ግለሰብ ትልቅ ነው። መለስ ዜናዊን እዩት፣ አል አሙዲን ተመልከቱት ኃይልና ሥልጣናቸው ገደብ የለውም። ፖለቲከኞች እንደመለስ ኢንቨስተሮች እንደ አል አሙዲ ትልቅ ለመሆን ይራኮታሉ። ስለዚህ “ሀ ራስህን አበልጽግ” ነው። ከዚህ በተረፈ ሰፊው ህዝብ ድሮም ትንሽዬ መንጋ ናት። ሰፊው ህዝብ ቁጥሯ እጅግ የበዛ ቢሆንም የሚያስፈልጋት ነገር ትንሽ ነው። ኑሮዋም በትንሹ ነው። ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ትንሽ ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር ካቀበሏት፣ አልፎ አልፎ ክትባት ከሰጧት፣ ሰፊው ህዝብ ከዚህ የባሰ ፍላጎት የላትም። የተወሳሰበ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ህግ አውጪ ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ የሚባል የሥልጣን ክፍፍል ወይም ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወይም የተገደበ ሥልጣን ያለው መንግሥት ወይም የፖለቲካ ፓርቲ…ፓርላማ… ነጻ ፕሬስ፣ ሰብአዊ መብት… ምናምን የሚባለው እንቶፈንቶ አያስፈልጋትም ደህና ቀበሌ ካልሆነም ጥሩ ፖሊስ ካደራጁላት ይበቃታል። ሰፊው ህዝብ እንዲህ ትንሽ በመሆንዋ ሁሌም ትናንሾ ይገዟታል።

ስለዚህ ይህ የገባን ሊቃውንት ዳር ሆነን እየበላን እየጠጣን እነዚህኞቹ እንዲህ አደረጉ እነዚያኞቹ ደግሞ እንዲህ አደረጉ እያልን የምናወራው የዚህ ስሜት ባለቤቶች ስለሆንን ይሆናል። እርግጥ ነው አንዳንዴ ስንዝናና መጠጥ ጎንጨት ስናደርግ መናገራችን አይቀርም። ወይም አንዱ ሁለት ታወቂ ሰዎች የታሰሩ ቀን በንዴት እንፈነዳና አሁንስ በዛ ብለን እናቅራራለን። ጣታችንን ቀስረን ቁጣችንን የምናበርድበት ተቃዋሚ ድርጅት ወይም ሌላ አካል ካለም እናፈላልጋለን። እንዲህ ስናደርግ ራሳችንን አንጠይቅም። አለመጠየቅ ብቻ ሳይሆን የዘመን ሰለባ፣ የቁሳቁስ ምርኮኛ፣ ሥልጡን ባሮች፣ ከአገር ብቻ ሳይሆን ከህሊናችን የተሰደድን ደካሞች መሆናችንን አናስተውልም። አፋችንን ዘግተን ብንቀመጥ ግልግል ነው። ማን ይምራን? ማን ያደራጀን? መሪዎቻችን ተከፋፈሉብን፣ ተቃዋሚዎቻችን ከዱን፣ እኛ መተባበር አልቻልንም…ዕድሜ ልኩን ይህን እየዘመረ እንደሚኖር ትውልድ የሚያስጠላ ነገር የለም። የተቆጣ ይቧደናል። ቁጭት ያለው ይደራጃል። ወኔ ያለው የሚያደራጀኝ አጣሁ ብሎ ራሱን ሆዱ ውስጥ ቀብሮ አይኖርም። መደራጀት የሚደራጀው ሰው ግዴታ ነው። ተከታይ ተገኝቶ መሪ አልጠፋም።

ዝምብሎ ክስ መደርደርና ራስን ሳያነጹ ማውራት አይገባም። በጥቅምና ሆዱ የሚንሸራተት በአወራሩ ብዛት ያስታውቃል። ወሬና ንግግር በዝቷል።

ዝም ብሎ ማውራት መተርተር ማውራት ነው። ማንም ስለምንም ጉዳይ ያወራል። በተለይ የፖለቲካ ከሆነ ማውራት ሁሉ የሀሰብ ነጻነት ነው። አታውቁም ማለት አታፍኑን ያስብላል ። ስለ እግዚሐብሄር መድረኩን ለቀቅ አድርጉት ሲባሉ አገሩ አሜሪካ ነው ይባላል። በተለይ የፈረንጅ አገሩ የኢትዮጵያውያን ፖለቲካማ ፈርስት ካም ፈርስት ሰርቭድ ነው። ቀድሞ የመጣ መድረኩ የሱ ነው። ቀድሞ የታወቀ ዘላለማዊነቱ አለቀ ደቀቀ ነው። አዳራሾች እንደሬስቶራንቶች ቋሚ ደንበኞች አላቸው። ለመታዘብም ለመተረብም ለመደበርም ለማዳነቅና ለሟሟቅም ወይም እዚያው አዳራሽ ውስጥ የሚሞት ወኔን አስፈንጥሮ ለአገሬ አንድ ነገር አድርጌላታለሁ ብሎ ራስን በከንቱ ለማጽናናትም የሚገኝ አይጠፋም። ወዳጄ ሆይ ከ እንዲህ ዓይነቱ መንጋ ተገኝተህ ከሆነ ውጣ! በነጻነት ታስብ ዘንድ ከመንጋው ፈቀቅ በል!

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios