እኛን የመሰለ መንግሥት?

ኢትዮጵያውያን ባንድ ነገር እንስማማለን – ብዙዎቻችን አደጋ ይታየናል። አደጋው የሚመጣው ከራሳችን ነው። ራሳችንን እየፈራን ነው። ብንሸነፍ በራሳችን፣ ብናሸንፍ ራሳችንን ነው። ገዢም ተገዢም እኛው ነን። ትግላችን ከራሳችን ነጻ ለመውጣት ነው። የአንድነት ጠላቶች የምናላቸውን ጨምረን አንድ ህዝብ ነን ብለን እናስባለን። ጠላትነትና ወንድማማችነት ተዛዝሎብናል። ከሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከገዛ ሀሳቦቻችን ጋር ፀብ ዝምድና አለብን። ከዚህ መታረቅና ማስታረቅ ያለብን እንዴት ነው ማለታችን አልቀረም።

ብሔሰባችንን ይዘን እርቅ ልንሰብክ አንችልም። ከብሔረሰባችን አንጻር ሆነን አንድነትነ ልንሰብክ አንችልም። ትግሬ ሆነነ የአማራና የትግሬን ጠብ መሸምገል አይቻለንም። ኦሮሞ ሆነን ኦሮሞና አማራን አንገላግልም። አማራ ሆነነ የአማራና የሶማሌን ችግር ለመፍታት ዳኝነት አንቀመጥም። ፀብ ዝምድና ካለን እንኳን ለዳኝነት ለሽምልግና አንበቃም። እኛው እንታረቅ ብሎም ነገር አልሰራም።

አለመስራቱን ያየን አርቲቡርቲው የሰለቸን ወገኖች ግን እንዲህ እያልን ነው:- ለአንዳችሁም ክብር አይኖረንም። የፈለጋችሁትን ሳይንስ ብታመጡ፣ የፈለጋችሁትን የነጻነት ቲዮሪ ብታመጡ፣ ጎሰኝነት ጎሰኝነት ነው። ክፍለሀገርተኝነት ተራና ኋላቀር ነው። በታሪክ ተፈትኖ የወደቀ አስቀያሚ ውጤት ያለው የፍጅት ድግስ ነው። ብዙነን፣ ምናልባትም 80 ነን ። 80ያችን ሰማንያ ቦታ አንቆምም። ትግሬ ላይ አስጠልቶ ጉራጌ ወይም ጎንደሬ ወይም ወለጌው ላይ የሚያምር ጎሰኝነት የለም። ካስጠላ ሁሉም ላይ ያስጠላል። ደስ ካለ ደግሞ ሁሉም ላይ ደስ ይላል። ደስ አለማለቱን ግን እያየን ነው። እኔ የዚህ ክፍለሀገር ልጅ ወይም ጎሳ አባል ነኝና የተሻልኩ ወይም ያነስኩነኝ ብሎ፣ ተለይቶ የሚኮራም ሆነ የሚያፍር እስኪ ብቅ ይበል!

ቡቱቶ ነው። ሞፈርና ቀንበር ነው። አቧራና ኮርኮንች መንገድ ነው። ከብት ማገድ፣ ሳር ቤት መኖር፣ ጭስ መጠጣት ሙጃሌ መፈንቀል ነው። በባዶ ሜዳ ተኮፋሽ ነው። እስክስታን ዳንኪራ ብቻውን ምግብ አይሆነንም። ባህላዊ አለባበስ ብሎ ጉራ ራቁቱን በሚሄድ ህዝብ ዘንድ ምንድነው? እርግጥ ነው ኢትዮጵያዊነት ሁሉ እንደዚህ አይደለም- ይህም ግን አለበት። ይህኛውንም መልካችንንም እንየው። እናሻሽለው እንጂ ደባብቀን አናሰማምረው። ከሚታይብን የሚነገርብን ያመናል። እንዲህም ሲባል ተሰደብን ብለን አጓጉል አንዝለል። የተለየ ኢትዮጵያዊነትን ራሳችን ላይ ጭነን ያንዱና አፍ ለማስያስዝም አንሯሯጥ። በዛሬው ኢትዮጵያዊነት ማፈር በትናንቱ ኢትዮጵያዊነት ከመቅናት ይመጣል። ከዚያ ውስጣዊ ንዴትና ቁጣም ይመነጫል። ኢትዮጵያዊነቱን ከጎሳው በላይ አብልጦ የሚወድም ኢትዮጵያዊነቱን ሲያሳንሱበት ወይም በውሸት እየካቡ ሲገድሉበት ደስ አይለውም። ይህ ደግሞ የግል ስሜት ነው። እንዲህ ያለ ስሜት ያለው ጎሰኛ ያልሆነ ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን መታወቅ አለበት።

ይሔ ኢትዮጵያን እንደካንሰር እየተከተለ የሚመዘምዛት የብሔር ብሄረሰብ.. ምናምንቴ መቅረት አለበት። ደግፈንም አዝለንም ተሸክመንም አየነው። ብሄር ብሄረሰቦች ብለን እሽኮኮ ብለን አየነው። አልሆነም። ይልቁንስ መንገድ ለሌላቸው መንገድ ይሠራ። ሆስፒታል ለሌላቸው ሆስፒታል እንሥራ። ዛፍ እንትከል። ዛፍ ዛፍ ነው። የዛፍ ወያኔ የዛፍ ቅንጅት የዛፍ ትግሬ የዛፍ አማራ የለውም። የሆስፒታል ኦሮሞ የግድብ አማራ የለውም። አንዱ እጃችን ዛፍ ይትከል። እኛ እውቀት ገብቶን ከመባላት እስክንነቃ ዛፉ ያድጋል። ጎጃም የተተከተለው ዛፍ ለትግሬ ዝናብ መሆኑ አይቀርም። ወለጋ የተሰራው፣ የኃይል ማመንጫ ግድብ፣ ጎንደር ላይ ያበራል። ይሄ እየተነጠሉ የእገሌ ልማት ማህበር ማለት ለሌላው የጥፋት ማህበር ነው። ምቀኝነት ያነግሳል። መንፈሳዊ ቅናት አያሳድርም። ውሸት ነው። በዚያ የተጀመረ ነገር ቀስ በቀስ ወደሥልጣን ጥያቄ ወደታሪክ ሽሚያ ያመጣል። የቅንፍ ኢትዮጵያዊነት ይቅር። የጥበብ ሳይሆን፣ የነገር አዛውንቱ፣ የወያኔው ማእከላዊ ኮሚቴ አባል፣ ስብሐት ነጋ ሰሞኑን የሰጡት መግለጫ እንዴት እንደሚያስጠላ ሰምተነዋል። መቸም በዚያች ሰዓትም ጠጥተዋል ማለት አይቻልም።

በየብሔረሰቡ ያላችሁ እንዲህ አይነቶቹ አባቶች እፈሩ! አዛውንቶች ይሰማችሁ! ትናንት የኢትዮጵያ የነበራችሁ ሰዎች ዛሬም የኢትዮጵያ ሆናችሁ ቀጥሉ። ሁላችንም ያን ስናደርግ ያነሱት እያነሱ ይመጣሉ። የጠበቡት እየጠበቡ ይመጣሉ። መጀመሪያ ከገዛ ሀሳባችን ነጻ እንውጣ። ራሳችንን የሚወክል በእኛ የተገደበ ሥልጣን የተሰጠው መንግሥት ይኑረን። ኢትዮጵያዊነታችንን አስቀድመን ኢትዮጵያዊነቱን ያስቀደመ መንግሥት እንሥራ። ከዚያ ጫማ እናድርግ። ከጭቃ ቤት እንውጣ፣ ይህን ለማድረግ እንነሳ። ኢትዮጵያዊነት ዝምብሎ በባዶ ሜዳ ማቅራራት አይደለም። መሬት ወድቆ የተገኝ ስምም አይደለም። ለዚያ መልሱ ላሊበላን አክሱምን ማን፣ ለምን፣ እንዴት፣ እንደሠራው ማወቅ ነው። ማንም ቢሠራውም እዚያች አገር ተሰርቷልና ጥበብ በዚያች አገር ነበር። የዛሬዎቹ ዘንድ ግን አንዲትም ጥበብ አልታየችብንም። ኢትዮጵያን ያለ አቅማችን ተሸክመናታል። ላሊበላን አይቶ እኛን ያየ እንዴት ያፍራል?

ኢትዮጵያዊነት ማንም መንደርተኛ የሚተረጉመው ተራ ስም መሆን የለሌበት ለዚህ ነው። ከወንዙ ከመንደሩ፣ ከጎሳው ውጪ፣ ሌላ ኢትዮጵያዊ ሊያይ የማይችል ሁሉ የአገር ጠንቅ ነው። አፄ ቴዎድሮስ ሸዋ ሲወርዱ ጎንደሬ ሆነው አይደለም። ዮሐንስ ጎጃም ሲመጡ ትግራይን ነጻ ለመውጣት አልነበረም። ምኒልክ አድዋ ሲወጡ ትግሬ ስለነበሩ አልነበረም። ኃይለሥላሴ አስመራ ሲሄዱ ኤርትራዊ ስለነበሩ አይደለም። ሰው ትልቅ አገር ተሸክሞ እንዴት ወርዶ ክፍለሀገሩ ውስጥ ይወተፋል?

ትንሹ ነገር ያገዳድለናል። ወንድሜን ገድዬ አሸነፍኩ ብሎ የድል ሐውልት የሚያቆም በኢትዮጵያ እየታየ ነው። ብዙ ሀበሻ የገደለ፣ የሀበሻ ጀግና በሀበሻ አገር ግሩም ሐልውት ይቆምለታል። የሰማእታት ሐውልት ይሉታል። ትላንትም እንዲሁም ነበር። የደርግ ወታደር፣ የሻእቢያ ወታደር፣ የወያኔ ወታደር… ሲባል ያለቀው የዛፍ ዓይነት እንጂ የሰው ህይወት ያውም የኢትዮጵያዊ አይመስልም። ዘራፍ አማራ ገዳይ፣ ዘራፍ ትግሬ ገዳይ፣ ብሎ መፎከርን የመሰለ አስቀያሚም አሳፋሪ ነገር የለም። ማፈርስ በዚህ ነበር የሐውትል ሱስ ካለብን ወንድማማችነታቸውን ሳያውቁ በስህተት ለተላለቁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የጋራ ሐውልት ልንሰራ እንችላለን። የቂም ሳይሆን የእርቅ ሐውልት ይሆንልናል።

ማንነትን በሌሎች ፊት እያነሱ፣ አመድ በዱቄት የሚስቅበትን ኩራት መውደድ ሄዶ ሄዶ ያገዳድል ካልሆነ አገር አራምዶ አላየነውም። በተለይ ተማርኩ በሚለው ሰው ላይ ሲታይና ሲሰማ ያስጠላል። አንድ ትምህርት ቤት ለመስራት ወይም አንድ በመከራ የሚያልቅ ወፍጮ ቤት ለመትከል ሲባል የሚረጭ የጎሳና የክፍለሀገር ልጅነት ፕሮፖጋንዳ ቦምብ ነው። እንዴት ሆኖ ሄዶ ሄዶ የተጋገረ ጎሰኝነት እንደሚወጣው ቆም ብሎ በድፍረት የሚያስረዳ አካል ያስፈልገናል። በአካባቢ ልጅነት ላይ የተመሰረተ የልማት ማህበር የጥፋት እንጂ የልማት ሆኖ አገር አልምቶ አላየነውም።

ጎሰኝነትና ኢትዮጵያዊነትን አጣምሮ መያዝ የግድ ከሆነ ሌላ ብዙ መንገድ ይኖረዋል። የወለጋ ልጆች ተሰባሰበው ጎንደር ያለውን ሆስፒታል እንሰራለን ቢሉ የጎንደር ልጆች አርሲ ሄደን እንገነባለን ቢሉ፣ የትግራይ ልጆች ሰሜን ሸዋ ውስጥ ምን የመሰለ ሆስፒታል እንሰራለን ቢሉ፣ ወሬውም ሥራውም ለአገር ይጠቅማል። ሥራው እንኳ ባይሰራ ወሬው ከሚሠራው ይበልጥ ልብ ማሞቁ አገር ማስታረቁ አይቀርም። ሌላው ግን ሥራውም ሳይሰራ ወሬው ብቻ አገር እየናደ ነው። ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት አንድ መገለጫ መልክ ያስፈልገዋል። ዝምብሎ አንድ እንሁን ማለት አንድነትን ያላመጣው ወሬው የለበጣ ስለሆነ ነው።

ለዚህ ሁሉ ማስታረቂያው ግልጽ ነው። ማንም ለማንም የማይነግረው አዲስ ቲዮሪ የማያስፈልገው ድርጊትን ብቻ የሚጠይቅ ተራና ነባር እውቀት ነው። በጎሳና አካባቢ ልጅነት የተደራጁትን የሚደግፉ የሚቃወሙትን ሁሉ አንምረጥ። በቋንቋና ጎሳ የተከፋፈለው ክልላዊነት ይቅር። ኢትዮጵያዊ ነህ፣ ግን ክልልህ ከዚህ በመለስ ነው ብሎ የተገደበ አገር መፍጠር ይቅር። በህግ የተገደበ ሥልጣን ያለው፣ ወጪ ወራጅ የሆነ መንግሥት እናቁም። የግለሰብ ነጻነት ይቅደም። ኢትዮጵያ ለሁሉም እንድትሆን ሁሉም አካባቢ ለኢትዮጵያውያን ክፍት መሆን አለበት። ሥልጣንም ልማትም፣ መኖሪያም፣ ቢዝነስም፣ መምረጥ መመረጥም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት መሆን አለበት። ካልተቧደኑ ብቻቸውን በሰውነታቸው መቆም ከሚፈሩ የቡድን ፖለቲካ አራማጆች ተጽእኖ ነጻ እንውጣ። ሰው በጎሳው ሳይሆን በዜግነቱ ብቻ የሚከበርበት አገር እንዲቆም የሚታገል ኢትዮጵያዊ ድርጅት ቢፈጠር መፍትሔ ይሆናል። ካለበለዚያ አርባ ጊዜ ብሔር ብሄረሰብ ብለው ቢያሰማምሩት ሲጠቃለል ውጤቱ ጎሰኝነት ከመሆን አይድንም። ያኛው የእነሱ ስለሆነ እዚያኛው ቤተክርስቲያን አልሄድም ማለትን የመሰለ ቆሻሻ ትንሽና ወራዳ የሆነ ተግባር የለም። ሺ ጊዜ ቢከራከሩ መደምደሚያው መከፋፈል፣ ቂም፣ አድማና እሱን የመሳሰሉትን ነገር ሁሉ ነው። ያውም በእግዜር ፊት በድፍረት ሲፈጸም የሚውል አልባሌ ነገር ነው። እኛን የመሰለ መንግሥት የተሰጠንም ለዚሁ ይመስላል።(ዘኢትዮጵያ)

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios