የግንቦት 8 መፈንቅለ መንግሥቱን በግንቦት 7 – የዋሽንግተኑ ስብሰባ


“ግንቦት 7/1997 በኢትዮጵያ በህዝብ ተመርጦ የተቋቋመውን ህዝባዊ መንግሥት ግንቦት 8 በተደረገውና በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በተመራ መፈንቅለ መንግሥት እንዲቀለበስ ተደርጓል” የሚል አገላለጽ የተጠቀሙት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ነበሩ። ዶ/ር ብርሃኑ ይህንን አባባል የተጠቀሙት በትላንትናው እለት በዋሽግንተን ዲሲ ድርጅታቸው ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ባዘጋጀው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ነበር። የስብሰባው ዓላማ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተሞክሯል ከተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ወይም ተሻሽሎ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ያነጣጠረ የግድያ ጥንስስ ነው ከተባለው ጋር ግንኙነት ሳይኖረው ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ነው። ወደ ስብሰባው አዳራሽ የመጣው አብዛኛው ህዝብ ግን ስብሰባውን ያገናኘው ወይም እንዲገናኝለት የፈለገው ሰሞኑን እየተወራ ካለው የመፈንቅለ መንግሥት ጉዳይ ጋር ይመስላል።

የሆኖ ሆኖ በዶ/ር ብርሃኑ ንግግር ውስጥ እንደተሰማው ስብሰባው ” ኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ “ የሚል አጠቃላይ አጀንዳ እንደተሰጠው መገለጹ ተፈነቀለም አልተፈነቀለም በመገልበጥ ላይ ያለ መንግሥት መኖሩን ያመነ ስበሰባ መሆኑ ያስታውቃል።ለዚህም ይመስላል ለረጅም ጊዜ ቀዝቀዝ ብሎ የነበረውን የዋሽንግተን ፖለቲካ ትኩሳትና ትንሳዔ የለቀቀበት የመሰለው የትናንቱ ስበሰባ የተዘጋጀው ወንበር ሞልቶ የቆሙ ሰዎች የሚታዩበት ሆኖ ነበር።ብዙ ሰው አይገኝም የሚል ግምት አዘጋጆቹ ዘንድ ያደረ መሆኑን ኋላ እየመጡ ከተደረደሩ ወንበሮች አንጻር መገመት ይቻላል።

በበርካታ ኃይለቃሎች የተሞላው ስብሰባ ዶ/ር ብርሃኑን ጨምሮ ሶስት ተናጋሪዎችን አስደምጧል። የመጀመሪያው ተናጋሪ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ነበሩ። የእሳቸው ንግግር ባብዛኛው በሞራልና አጠቃላይ የስነምግባር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን ቀጥሎ የተናገሩት የህግ ባለሙያው አቶ ፍሬሕይወት በዳኛነትና በፍትሕ ሥርዓቱ ዙሪያ ያለውንና መሆን በሚገባው ላይ አተኩረዋል።

የዶክተር ብርሃኑ ንግግር “የኢትዮጵያ ጉዳይ አማራጭ እስከ ሌለለው ድረስ እየወደቅንም እየተነሳንም ከጥፋታችን እየተማርን የተለያዩ የትግል ስልቶችንና የድርጅት አማራጮችን እያፈላለግን የተከፈለውን መስዋእትነትን ሁሉ ከፍለን አገራችንን እናስከብራለን ከማለት ሌላ አማራጭ የለንም።” የሚል መንደርደሪያን መሠረት ያደረገ ሆኖ “ይህን ከተረዳን ለአገራችን ህልውናና ለሁላችንም ደህንነት መጠበቅ እያንዳንዳችን የድርሻችን ማበርከት ይኖርብናል እላለሁ” የሚል ማሳሳቢያ ይዟል። በዚህ የተስማሙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተለይም አገር ቤት ውስጥ ንቅናቄ መጀመራቸውን አያይዘው መግለጽ የፈለጉ መሆኑን ከጠቅላላው የንግግራቸው ይዘት መገንዘብ ይቻላል። የአዲስ አበባውንም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የለንበትም ማለታቸው ደጋግመው የተገለጸ ቢሆንም የትናንቱን ንግግራቸውን አያይዞ ለተረዳ ሰው አልነበሩበትም ብሎ ለመናገር ሳይቸገር አይቀርም። በተለይ “ገና ምኑን አይተውት እናሳያቸዋለን!” የሚለው አገላለጻቸው ለጥርጣሬው ፍንጭ በር መክፈቱ አልቀረም።

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዋል ተብለው የተያዙት ሰዎች ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ስላላቸው ግንኙነትና (የድርጅታችሁ አባል ናቸው ወይ በሚል) ስለተነሳው ጥያቄም ዶ/ር ብርሃኑ የሰጡት መልስ “ማን የግንቦት 7 አባል እንደሆነና እንደሆነ አላውቅም” የሚል መልስ ነው። እንደሳቸው አባባል ድርጅቱ የሚሰራው በህቡእ ስለሆነና አደረጃጀቱም አንዱ አንዱን እንዳያውቅ ሆኖ ስለሆነ ከታሰሩ ሰዎች ውስጥ አባል የሆኑም ያልሆኑም ሊኖሩ ይችላሉ።
ቀሪውንና ሰፊውን ዘገባ በሚቀጥለው ሳምንት በሚወጣው የዘኢትዮጵያ ጋዜጣ ይዘን እንወጣለን።

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios