ፍሬ ነገር

በሠፈራው መርሃ ግብር – ጎንደር ትግራይ ሄዶ ቢሠፍር ምን አለበት?

በሰሜን ጎንደር በዘንድሮ የሠፈራ መርሀ ግብር ከ50ሺህ በላይ አባዎራዎችና ቤተሰቦቻቸውን ተቀብሎ የማስፋር እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ ምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ማስታወቁን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ሆነ እሱን ጠቅሶ የጻፈው ሪፖርተር ጋዜጣ አስታውቋል። የዓለም ኢኮኖሚ እንኳ በወደቀ ጊዜ እየተፋፋመ ባለው የኢትዮጵያ ልማት ተቋዳሽ ያልሆኑት የጎንደር አርሷ አደሮቹ ከትውልድ ቀያቸው ተነቅለው ወደ ተሻሉ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ እየተደረገ መሆኑን ተነግሯል። በኢህአዴግ ፖሊሲ፣ ሠፋሪዎች፣ ቋንቋን መሠረት አድርጎ በተከለለው አዲሱ የፌደራል ክልል መሠረት፣ ክልል ተሻግረው መሄድ የማይችሉ ብቻ ሳይሆን ፣ሰፈራው ራሱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ሲወገዝ ከነበረው የደርግ ሠፈራ ልዩ እንደሚያደርገው የመንግሥት ባላሥልጣናት በኩራት ይናገራሉ። ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጵያ የሠፈሩ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራው ክልል አርሶ አደሮች ከስፈሩበት ተነስተው ወደመጡት እንዲመለሱ ትርምስ መፈጠሩንና በዚህም ሳቢያ የገዛ ፖሊሲውን ጥሶ ክልል እያሻገረ ያሰፈረውን ኢህ አዴግን ተፈታትኖት እንደነበር አይዘነጋም። የዚያ ዓይነት ችግር እንዳይደገም በመስጋት አሁንም በመሬት ጥበት ጭምር የተጨናነቁትን የሰሜን ኢትዮጵያ አርሷ አደሮች እንደሚቆላ ቡና እዚያ በዚያው እያገላበጠ ማስፈሩን እንግዲህ ምን ይደረጋል እንደሚባል አማራጭ የያዘው ይመስላል። መሬትን አሳልፎ የመስጠት ቸርነቱ ያልተጓደለበት ኢህአዴግ ዘንድሮም የኢትዮጵያን ለም የእርሻ መሬትን ለሱዳን ሰጥቷል እየተባለ በወቀሳ ብቻ በታለፈበት በዚህ አካባቢ ነዋሪዎችን እያፈናቀልኩ ሠፈራ እልካለሁ ብሎ መናገሩ ማስገረሙ አይቀርም። የሆኖ ሆኖ በሠፈራ ስሙ ተነስቶ በማያውቀው ጎንደርን ሳይቀር በመተማ፣ በጠገዴ ፣ በታችና በምእራብ አርማጭሆ እንዲሁም በቋራ አካባቢዎች ወስጄ አሰፈራቸዋለሁ ማለቱ ክልልን በክልል እዚያው በዚያው ማገላበጡ በመሆኑ ፖሊሲው ስለሆነ ምንም አይደለም። ለእያንዳንዱ ሰፋሪ 500 ካሬ ሜትር መሬት እሰጣለሁ ማለቱም እንኳን ለኢትዮጵያዊ ለጎረቤት አገርም የሚሰጥ ነውና ማለፊያ ነው። ግን በቂ ለም መሬት አለ ወይ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ምክንያቱም እንደሚነገረው ከሆነ ይኸኛው የሠፈራው መርኻ ግብር አንዱ አካል ነው። በየደረጃው ይቀጥላል። ያ ማለት ደግሞ እስካሁን የሠፈሩትን እንኳ እንደሚባለው ከ125ሺ አባወራዎች በላይ የጎንደር አርሶ አደሮች ሳንዘነጋ መጪዎችን ደምረን ስናስበው ቁጥሩ መብዛቱ አይቀርም። ሠፈራም ሲባል 500 ካሬ ሜትር ብቻ ወርውሮ ዞር የሚባልበት ነገር አይደለም። ከመሬቱ የመልማት አቅም አንስቶ እስከ አርሶ አደሩ አቅም ድረስ ያሉትንና ሌሎችንም በመፈናቀልና በመስፈር የሚመጡ ማህበራዊ ቀውሶችን ሁሉ ያካታታል። በስተጎንደር ያለ መሬት ለሱዳን ተሰጠ ወይም ወደ ሌላ ክልል ተጠቃለለ እያስባለ ጧት ማታ ልማቱ የሚነገርለትን የቀድሞው የጎንደርን እርሻ ግዛት ሁመራና ሰቲትን ጥያቄ የሚያስነሳው እንዲህ ያለው ችግር ጭምር ነው። ሁሉንም ነገር ዝምብሎ የጎሳና የጥላቻ ፖለቲካ ያመጣው ትችት ነው ብሎ ማጣጣሉ እየዋለ ሲያድር የሚያጣጥሉትን ሁሉ መጣሉ አይቀርም። ከዚህ ይልቅ ይህን ሲመች ሲመች በቋንቋ ሳይሆን ሳይሆን ደግሞ ያለቋንቋም ጭምር እንዲካለል የተደረገውን አገር ብሎም ከፋፋዩን የፈደራሊዝምና የክልል ፖለቲካናን መርምሮ ኢትዮጵያውያን ሁሉም አገራቸው ሆኖ አገሬ ነው ብለው ለሞቱለት ለም መሬት ሁሉ በእኩልነት ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ቢመቻች ጥሩ ነው። በክልሉ የማያውቃት ባድመ ሄደችብኝ ብሎ ሄዶ የሞተን ሰው ስትኖር ግን እዚያው በክልልህ ኑር ማለት ምን ማለት ነው? አሁን ለምሳሌ የጎንደር አርሶ አደሮች እንኳን ትላትን የራሳቸው የነበረውና ዛሬ ለትግራይ እንደተከለለው ሁመራ አይነቱ ቦታ ቀርቶ ሰሞኑን አቶ መለስ ዜናዊ ራሳቸው ተገኝተው በምርጥ የልማት አርበኝነት ተደስተው ከሸለሟቸው የትግራይ አርሶ አደሮች ጋር አብረው ቢሰፍሩ ምን አለበት? የጥላቻ ፖለቲካው የሚቀረው እንዲህ ባለው የፍቅርና የመተሳሰብ ፖለቲካ ሲኖር ጭምር ነው። ትግራይ ጎንደር መጥቶ ከሰፈረ ጎንደርስ ትግራይ ሄዶ ቢሰፍር ምን ነውር አለበት?

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios