በአዲሱ አዋጅ ያልተመዘገቡ ጋዜጦች ይሰረዛሉ

የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ መሰረት ያልተመዘገቡ ጋዜጦችና መጽሔቶች ከአምስት ቀናት በኋላ ይሰረዛሉ ተባለ። ከ57 ጋዜጣና መጽሔቶች እስካሁን ቀርበው ፎርም የሞሉት 22 ሲሆኑ ሰርትፊኬት የተሰጣቸው ሰባት ብቻ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሮድ ካስት ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ደስታ አስፋው እንደገለጹት የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ መሰረት አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የተቋቋመ ማንኛውም ፕሬስ አዋጁ ከፀናበት ህዳር 25 ቀን 2001 ጀምሮ ባሉት ቀጣይ 90 ቀናት ውስጥ መመዝገብና የምስክር ወረቀት ማግኘት አለበት። እስካሁን 48 ከሚሆኑት የመንግሥት፣ የማህበር፣ የኃይማኖትና የፖለቲካ ድርጅት ልሳናትን ሳይጨምር 22 የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ቀርበው ፎርም መሙላታቸውንና ለሰባቱ ሰርትፍኬት መሰጠቱን ም/ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከየካቲት 25 ቀን 2001 በኋላ የሚመጣን አመልካች ባለሥልጣኑ እንደማያስተናግድና በአዋጁ መሰረትም እንደሚሰረዝ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ 74 ጋዜጣና መፅሔቶች ያሉ ሲሆን 57ቱ የግል ናቸው። (ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ)

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios