መንግሥት 4.9 ሚሊዮን ህዝብ ተርቧል አለ

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የምግብ እጥረት 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ ዛሬ ለአገር ውስጥና ለውጪ አገር ጋዜጠኞች እንደገለጹት መንግሥት ከለጋሽ አገሮችና ድርጅቶች ጋር ባደረገው የመስክ ጥናት ለችግሩ የተጋለጡ ዜጎች ብዛት 591 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ ያስፈልጋቸዋል።

የምግብ እጥረቱ ሊከሰት የቻለው ባለፈው ዓመት አጋጥሞ የነበረው የበልግ ዝናብ እጥረትና መዛባት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የምግብ ዋጋ መናር የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንዳንድ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ያጋጠሙ የእንስሳት ግጦሽ እጥረትና ይህንኑ ተከትሎ የተከሰተው የእንስሳት ዋጋ መቀነስም ለእጥረቱ በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ በጥናቱ መረጋገጡን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለማቃለል ለምግብና ምግብ ነክ ላልሆኑ ጉዳዮች ከስድስት እስከ 10 ወራት የሚዘልቅ እርዳታ ለማቅረብ ከ602 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ መንግሥት በመጠባበቂያነት ከያዘው 148 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በእጁ እንደሚገኝና ቀሪውን 455 ሚሊዮን ዶላር ለማሟላት ከለጋሾች እንደሚጠበቅም መናገራቸውን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios