የቤተመንግሥቱ ጄነራል- ፍሬሰንበት

ብርጋዲየር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ የአሁኑን ጨምሮ በቀደሙት ሁለት መንግሥታ የብሔራዊ ቤተመንግሥቱ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ሠርተዋል። ሶስቱም መንግሥታት ከቤተመንግሥት ያላስወጧቸው ሰው ነበሩ።
ንጉሡም ኮ/ል መንግሥቱም አቶ መለስ ዜናዊም ብርጌዲየር ጄነራል ፍሬሰንበትን ከቤተመንግሥት እንዲለዩ አልፈቀዱም። ፍሬሰንበትን ከቤተመንግሥቱ የለያቸው ሞት ብቻ ነው። አሁን በቅርቡ ጥቅምት 16/2001 አርፈዋል።

ከ30 ዓመታት በላይ ቤተመንግሥት የኖረ እንዲህ ያለ ባለሟል መችም የሚያወራውም ሆነ የሚወራለት ወግ አያጣም።

አንድ ቀን ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር በመኪና ሆነው ወደደብረ ዘይት መንገድ ያቀናሉ። ሁሌም እንደሚደረገው አንድ የአካባቢው ተወላጅ ባላገር የጃንሆይን መኪና አስቆሞ እጅ ከነሳ በኋላ አቤቱታ ሊያሰማ ይጠጋቸዋል።ንጉሠ ነገሥቱ መስኮታቸውን ወረድ አድርገው ከውጭ የሚያናግራቸውን ለመስማት ተዘጋጁ። ሰውዬ በኦሮምኛ ቋንቋ አቤቱታውን ማሰማት ጀመረ።

በዚህ ጊዜ እኔ አብሬያቸው መኪና ውስጥ ነበርኩ። እኔ ቋንቋውን ሰላማላውቅ ዝም አልኩ። ጃንሆይ ወደኔ ዞር አሉና “ያናግርሃልኮ እኮ ለምን አትመልስለትም?” አሉኝ። “ጃንሆይ ኦሮምኛ አላውቅም!” አልኳቸው። በያዙት ዱላ ሆዴን ነካ ነካ እያደረጉ ፈገግ አሉና “ የውጭ አገር ቋንቋ ከማጥናትህ በፊት የአገርህን ቋንቋ ብታውቅ አይሻልም ነበር?” አሉኝ። እሳቸው ግን በኦሮምኛ አነጋገሩት። ሰውየውም ቀጠሮ ተያዘለት።

ጄነራል ፍሬሰንበት ይህ በጣም ከሚያስገርማቸው ነገር አንዱ መሆኑን ያስታውቃል። አዲስ ዘመን ጋዜጣና ሪፖርተር መጽሔትን ጨምሮ በተለያዩ ቃለመጠይቆቻቸው ላይ ይቺን ነገር ደጋግመው ያነሷታል። ጄኔራል ፍሬሰንበት በጠቅላላው ለ65 ዓመታት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሹን ያሳላፉት በቤተመንግሥት ነው። ጄነራል ፍሬሰንበት ባሳለፉት የረጅም ዓመታት የቤተመንግሥት ኃላፊነታቸው፣ የቤተ መንግሥትን ብሔራዊ ሀብትና ታሪካዊ ቅርስነት በመገንዘብ ወደ ብሔራዊ ሙዚየምነት የመለወጥ ውጥን ጅምራቸውን ሳያጠናቅቁ አልፈዋል። ይሁን እንጂ ጄነራል ፍሬሰንበት ቢያልፉም በመንግሥታት ለውጥ ከጥፋት ያዳኑትን ታሪካዊ ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ መሠረት ጥለዋል።

ባለፉት ሶስት መንግሥታት ይህን የተለየ ክብርና ፍቅር ያሳደረባቸው መሆኑን የሚናገሩለትን ብሄራዊ ቤተመንግሥት በታሪካዊ ቅርስነቱ የሚጎበኝ ልዩ ሥፍራ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽ አድርገዋል። የነገሥታትን በበተለይም ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ያሉትን የወግና የማእረግ ቁሳቁሶች አልባሳትና ተሽከርካሪዎች አሰባስበዋል። ከ1948 ጀምሮ የተሰራው ቤተመንግሥት የተለያዩ መሪዎች ቢፈራረቁበትም ቤተመንግሥቱ ግን የያዘውን ቁሳስቁስ እንደያዘ አሁን ድረስ አለ። በተለይም የንጉሠ ነግሥቱ መኝታ ቤት አልጋው እንድተነጠፈ እቃው እሳቸው ይኖሩበት እንደበረው ሆነ የተቀመጠ ነው። የግርማ ልቦስቻቾው፣ መጫሚዎቻቸውና የራስ ቆቦቻቸው አሁንም ዛሬ እንደሚያገለግሉ ሆነው ተቀምጠዋል። እነዚህን ሁሉ አንዳችም ጉድለት ሳይደርስባቸው ተካላክለውና ኃላፊነቱ ወስደው በወግ የጠበቋቸው ጄነራል ፍሬሰንበት ናቸው። ጄነራሉ ይህን ሲያደርጉ ፈተና አልነበረባቸውም አልደረሰባቸውም ማለት አይደለም። የቤተመንግሥቱ ውድና ብርቅ እቃ አንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችን ማጓጓቱ አልቀረም። ለምሳሌ አንድ ቀን እንዲህ ሆነ።

ደርግ ሥልጣን እንደያዘ፣ በ1968 ዓም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደርጉ ዋና ሊቀመንበር ብ/ጄነራል ተፈሪ ባንቲ አማካይነት በተጻፈውና ለቤተመንግሥት (ለሳቸው) በግልባጭ በደረሰው ደብዳቤ አንድ ትእዛዝ ይተላለፋል። ደብዳቤው የንጉሡ መገልገያ የነበሩትን “ሮልስ ሮይስ” አውቶሞቢሎች በእንግሊዝና በፈረንሳይ ለኢትዮጵያ አምባሳደሮች እንዲሰጥ የሚያዝ ነው። አምባሳደሮቹ በእነዚህ መኪኖቹ ሆነው ቢታዩ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ ያደርገዋል የሚል ነበር ምንክንያቱ። ጄነራል ፍሬሰንበት ትእዛዙን እቀበላለሁም አልቀበልምም ሳይሉ ጄኔራል ተፈሪ ባንቲን ሲያገኙ በቀጥታ ያነሱባቸዋል።
ለካ ህዝቡ ወታደሮች ምንም አታውቁም የሚለን እውነቱን ነው…
ምን ማለትህ ነው? ይላሉ ጀኔራል ተፈሪ
እንዴ! የአገር ቅርስ እንዴት አድርገን ነው ወደ ውጭ አገር የምንልክው። ይህ መኪና የተሰጠን ከእንግሊዝ ህዝብና መንግሥት ነው። ንብረትነቱም የህዝብ ነው። አሁን ተመልሶ እንግሊዝ ተወስዶ ቢታይ ለስጦታው ዝቅተኛ ግምት መስጠት አይመስልም? ደግሞስ ለአምባሳደር መርቸዲስ መች አነሰውና ነው ከኢትዮጵያ ሮልስ ሮይስ የሚሄደው?

ጄኔራል ተፈሪ በሀሳቡ ተስማሙና መኪኖቹ በባእድ እጅ ከመግባት እጅ ዳኑ። የተባሉትም አምባሳደር መንግሥታቸውን የከዱት ወዲያ እንደነበር ተጽፏል። መኪኖቹ ግን ዛሬ በቤተመንግሥቱ በሙዚየምነት ተቀምጠዋል።

ደግሞ ሌላ ቀን አንደኛው የደርግ አባል ከእንግሊዝ መንግሥት ለአፄ ምኒልክ በ1800ዎቹ መጨረሻ የተላከለውን የወርቅ ትሪ እዲሰጠው ያዛል። ጄነራሉ እነዚህማ ታሪክ ናቸው ቅርስ ናቸውን አይሰጡም ይላሉ። የደርጉ ሰው “አሁንም አልጋወራሽን እየጠበቁ እንዴ?” ብለው በአሽሙርና ቁጣ ይናገሯቸዋል። አብዮቱ የፈነዳበት ጊዜ ስለነበር ነፍስ በቀላሉ የምትፈነዳበት ጊዜ ነበር። እንደዋዛ መገደል አለ። ጄነራሉ ቢፈሩም እሺ አላሉም። “ይሄ የአገር ታሪክና ቅርስ የሆነ ውድ እቃ ነው! በሚለው አቋማቸው ጸኑ። እንዲህ በማድረጋቸውም እሳቸው የሰውና የመሪዎች ሳይሆኑ “ እኔ እቃ ጠባቂ ነኝ” የሚል መልስ ሰጡ። በእንቢታቸው ተከሰሱና የደርጉ ሊቀመንበር ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ዘንድ ቀረቡ። ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ጠየቋቸው። የሆነውንና ያሉትን ደግመው አስረዱ። ጄነራሉ ልክ ናቸው ከዛሬ ጀምሮ ማንም በቤተመንግሥቱ ጉዳይ ማንም እንዳይገባባቸው ተባሉ።

ደግሞ ሌላ ጊዜ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጄነራል ፍሬሰንበት አንድ ቀን ይጠሯቸውና በቤተመንግሥቱ አጥርና በየግድግዳው ያለውን የዘውድ ሥዕልና ምክልት ሁሉ እንዲያጠፉ ያዟቸዋል። ፍሬሰንበት ትእዛዙን ተቀብለው ይወጣሉ። ምንም ሳያደርጉ ዝም ብለው ይጠባበቃሉ። ሌላ ጊዜ ቆይቶ መንግሥቱ ትዝ ሲላቸው እንደገና ተቆጥተው “ያልኩት ለምን አልተፈጸመም ይሏቸዋል።?” “ቤተመንግሥቱ የተሠራው በልዩ ባለሙያዎች ነው። ስለዚህ ሲፈርስም ባለሙያ መሐንዲስ ያስፈልጋል። እንደገና ለመጠገንም ሆነ ሲፈርስ ገንዘብ ስለሚያስፈልግ የገንዘብ ሚኒስቴር ሰው ያስፈልጋል። የትኛው መፍረስ የትኛው ለታሪክ መቀመጥ እንደሚያስፈልግ መሆኑን የሚያውቅ የታሪክ ሰው ያስፈልጋል። እነዚህ በሌሉበት ሁኔታ ብቻዬን ማስፈረስ ከብዶኝ ነው።” እያሉ ምክንያት ደረደሩ መንግሥቱ ምንም አላሉም። ዝም ብለዋቸው ሄዱ። ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ታሪክ ሆኖ ቀረ።

የመንበረ መንግሥቱ ዙፋን፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት የወግ እቃዎች፣ ነገሥታቱ የሰበሰቧቸው ቅርሶች፣ የከበሩ ድንጋዮችና ጥንታዊ መጽሐፍት፣ አልባሳትና ጌጣጌጦችና ተሸከርካሪዎች አሁንም በቤተመንግሥቱ ይገኛሉ። ንጉሠ ነገሥቱ ያን ሁሉ ነገር ትተውና ከዚያም ተነጥለው ሲወሰዱ ማየታቸው ሁሌም የሚያሳዝናቸው ታሪክ መሆኑ ሲናገሩ እንደነበር ተጽፏል። ጃንሆይ እስር ላይ በነበሩበትም ጊዜም የሚቀርብላቸው ምግብ እንዳይጓደል የሚወዱትን በማቅረብ የቻሉትን ያህል እንክብካቤ በማድረግ ረገድ የቻሉትን ሁሉ ማድረጋቸው የህሊና እረፍት እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል። ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ሲገባም ጄነራል ፍሬሰንበት እዚያው ቤተመንግሥት ጊቢ ውስጥ ነበሩ። ኮ/ል መንግሥቱ ቤተመንግሥቱን ትተው ሲሄዱ አንዳችም ነገር አለመንካታቸውን ይመስክሩ እንደነበር ተስምቷል። ኢህአዴግም የገባ ጊዜ አንዲት ሴት ታጋይ ወደ ቤተመንግሥቱ አስተዳደር ጽ/ቤት በመሄድ ጀኔራሉ የት እንዳሉ አሳዩኝ እያለች ስታፈላልጋቸው ግራ የተጋቡት ሠራተኞች ምን ልታደርጋቸው ነው ብለው ሰግተው ነበር። እሳቸውም ዞር እንዲሉ ቢነገራቸውም መቸም በህይወት እያለሁ በሚል የኖሩለትን አደራ ሸሽተው መሄድ አልፈለጉም። እንደምንም ተጋፈጧት። ታጋይዋ ሴት ግን እንዳገኘቻቸው ያለቻቸው ተቃራኒውን ሆኖ ተገኘ። “ጄነራል አይዞት እኔና እርስዎ ሆነን ይህንን ሥፍራ እንጠብቃለን አንዳችም ነገር አይደርስምና ስጋት አይግባዎት!” ጄነራሉ ማመኑ አልቻሉም። የቤተመንግሥቱ እቃ በሙሉ ወደትግራይ ተጉዟል ተብሎ የተጻፈው ሁሉ ሀሰት መሆኑን ተናግረዋል።

ጀኔራል ፍሬሰንበት ባለፉትም መንግሥታት ሲያደርጉት እንደኖሩት ሁሉ የኢትዮጵያ እንግዳ ሆኖ ወደዚያ ቤተመንግሥት የሚመጣውን ሁሉ እየተቀበሉ በቤተመንግሥቱ ሲያስተናግዱ ኖረዋል።የኢትዮጵያ መሪዎች ተቀብለው በርካታ የውጭ አገር መሪዎችና ባለሥልጣናትን ተቀብለው ሲያነጋግሩ እሳቸው ደግሞ ተቀብለው ያስተናግዳሉ። ፕሬዚዳንት ግርማና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወደ ቤተመንግሥቱ እንግዳ በመጣ ቁጥር “ይህን ሁሉ ቅርስ ያቆዩ እሳቸው ናቸው” እያሉ ከእንግዶች ጋር ስለሚያስተዋውቋቸው እስከዛሬ ሲያሰባስቡ የኖሩት ታሪካዊ ቅርስ ሁሉ ወደፊትም በዚሁ መልክ እንደሚቀጥል ተስፋ ያሳደረባቸው መሆኑን ተናገረዋል።

ብርጋዲዬር ጄኔራል ፍሬሰንበት አምዴ ከእናታቸው ከወይዘሮ ወሰንየለሽና ከአባታቸው ቀዥ አዝማች አምዴ ማንያደርሳል ጥር 12 ቀን 1922 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ።

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፣ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት፣ ቀጥሎም በመድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ተከታተሉ። ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል በመግባት፣ በመኮንንነት ከተመረቁ በኋላ፣ በናቪጌተርና በኮሙዩኒኬሽን በራሪነት፣ እስከ ብርጋጌድየር ጄነራል ባሉት፣ ከፍተኛ የመኮንንነት ማእረግ አገራቸውን በክብር አገለግለዋል።

ጀኔራል ፍሬሰንበት፣ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የአገልግሎት ዘመናቸው፣
የምድር የቴክኒክ ትምህርት ረዳት ኃላፊ፣ የአስተዳደር ክፍል ዋና ኃላፊ፣
የደብረዘይት አየር ሃይል ጣቢያ ዋና አዛዥ፣ በጦር ሃይሎቸ ቺፍ ስታፍ ቢሮ የአየር ሃይል
ተጠሪና የአየር ሃይል ጂነራል ኢንስፔክተርነት ዋና ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።

በዚሁ አገልግሎታቸው ላይ እንዳሉ አሜሪካን አገር ከሚገኘው “ብላክ ስቶን ስኩል ኦፍ ሎው” በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኘተዋል። እንዲሁም በእንግሊዝ አገር፣ የአየር ኃይል ጄነራል ኢንስፔክተርነትና የተለያዩ የአስተዳደር ኮርሶችን ወስደዋል።

ጄኔራል ፍሬሰንበት፣ በ1964 ዓም ከአየር ኃይል ክፍል ወደ ቤተመንግሥት ተመድበው ፣ በእልፍኝ አስከልካይነትና በፕሮቶኮል ክፍል ረዳትነት ለሶስት ዓመታት አገልግለዋል። አገልግሎታቸውንም እንደጨረሱ፣ ወደ ክፍላቸው መመለስ ሲገባቸው፣ በሥራ ታታሪነታቸው ተመርጠው፣ በቤተመግሥት እንዲቆዬ፣ በንጉሠ ነገሥቱ በመታዘዛቸው፣ የኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ዋና አስተዳዳሪ ሆነው፣ ሐምሌ 13/1966 ተሹመዋል። የደርግ መንግሥት ከመጣ በኋላም፣ ሐምሌ 19/1968፣ የብሔራዊ ቤተመንግሥት ዋና አስተዳዳሪ በመሆን በብርጋዴየር ጄነራልነት ማዕረግ ሲሰሩ ቆይተዋል። ጄነራል ፍሬሰንበት ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በዚያው ኃላፊነትቸው ከ700 ሠራተኞች በላይ ያለውን የቤተመንግሥት አስተዳደር በመምራት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት ሶስት ልጆችና፣ አምስት የልጅ ልጆችን ያፈሩ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ባደረባቸው ህመም እዚሁ አሜሪካን አገር በህክምና ሲረዱ ቆይተው ጥቅምት 16/2001(ኦክቶበር 26/2008) በተወለዱ በ83 ዓመታቸው አርፈዋል።

ኦክቶበር 31/2008 በተፈጸመው የቀብር ሥነሥርዓቱ ላይ ፓትሪያርኩን ጨምሮ የጠ/ሚር ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው መገኘታቸው ተዘግቧል፡፡

(በዚህ ጽሑፍ የተከታቱ መረጃዎች በሙሉ የተወሰዱት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ከሪፖርተር መጽሔት፣ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ካልታተመው የጄነራሉ የግል ማስታወሻ እንዲሁም ከዜና እረፍታቸው እትም ነው- ዘኢትዮጵያ)

1 Comment for “የቤተመንግሥቱ ጄነራል- ፍሬሰንበት”

  1. Yadesa Bojia

    Wonderful story, almost two years ago, I was invited to meet with the president The honorable major Girma. After our meeting the president allowed me to visit the bedroom of Emperor Haile Selassie and Queen Menen. I was with my wife and my sister and we were very impressed how they kepy the place neat and intact. Even the bed was just the way they left it. Waht impressed me the most was how simply the emporor lived and all his cloth and shoes was made locally. I grew up in the time of derg and what I saw was clearly different than what is told to me. Thnak you fot all three governments to keep our history intact.

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios