ህዝብ አላህ!

ሂዝቦላህ ማለት- “ህዝብ አላህ!” ማለት ነው- እኛ የአላህ ህዝብ ነን እንደማለት ነው ብሎ ትንታኔ የሰጠ ሰው መኖሩ ተሰምቷል። በፖለቲካ ጨዋታ መካከል ትንታኔ መስጠት የእያንዳንዱ ስው የንግግር መብት ነውና ዝምብሎ መስማት ዴሞክራሲያዊ ግዴታ ነው። ሂዝቦላን በውስጡ አዝሎ የኔ ነው ወይንም አይደለም ማለት አቅቶት ግራ የተጋባው የሊባኖስ ህዝብም ከኑግ እንደተገኘ ሰሊጥ አብሮ ሲወቀጥ ዓለም እያየ ነው። ሊባኖስ በቁጭት ውድመቷን እያየች ለዓለም ትጮኻለች። ልዋጋ እንዳትል ሮኬቶቹን ወደ እስራኤል አልተኮሰችም። የተኮሰው ሂዝቦላ ነው። ዝም ልበል እንዳትል እየወደመች ያለችው ራሷ ናት። ሂዝቦላን እንዳትናገር “ላም እሳት ወልዳ…” ሆነባት። በዚያ ላይ አለ አይደል ሂዝቦላምኮ ቢሆን ሀቅ ይዟል…

ገዳይና አሳሪ ሆኖ የትግራይን ህዝብ ከኢንተርሃሙዌይ ለመታደግ ትግራይ ልጆች መካከል የመሸገው ወያኔም እንደ ሂዝቦላ ሀቅ ባይኖረውም ጦሱን ለዚያ ህዝብ ማትረፉ አልቀረም። እስራኤል ራሴን ለመከላከል በምወስደው እርምጃ ሁሉ ወላ ሂዝቦላ ወላ ሊባኖስ ወላ ህጻን ልጅ ወላ ሴት ልጅ ሳልል ሊባኖስን ከመደብደብ ትንፋሽ እንኳ አልወስድም ብላለች። እዚህም እንዲሁ ወያኔና የትግራይ ልጆችን በቀላሉ ለይተን እንዳናይ ዝላዩ በዝቶብናልና ምንም ማድረግ አንችልም የሚል አካሄድ መኖሩ ይታያል። በአስመራ ወይም ቢያስፈልግም በሶማሌ አድርገን ብቻ በተገኘው መንገድ ሁሉ ወያኔን ማጥፋት አለብን ብሎ የሚማከር ጎበዝ የለም ብሎ መማል ድርቅና ከመሆን አያልፍም። ይህ መንገድ ልክ ነው ልክ አይደለም ብሎ ለማሰብ ግን አሜሪካ ውስጥ የሚዘሉትን የወያኔ መንግሥት ደጋፊዎች ሳይሆን ያንን ድምጹ የማይሰማውን ሰፊውን የትግራይ ሕዝብ ማሰብ ይገባል።

የትግራይ ህዝብ በወያኔ የተካደ ብቻ ሳይሆን “ጎሰኛ” እየተባለ በደናቁርት የፖለቲካ ጠበብቶች እንዲሰደብ ወካይ ሆነው የቀረቡት “ጎሰኞች” ለህዝባቸው ያለ ስሙ ስም ያሰጡት ጎጂ እንደራሴዎች ናቸው። ህዝብ ጠባብ አይደለም። ጠባቦች ሁሌም በህዝብ መነገድ የሚፈልጉ እናውቅልሃለን የሚሉ ምንም ውክልና ሳይኖራቸው በጎሳ እየተጠራሩ ሥልጣን ለመያዝ የሚሮጡ ወይም የያዙ ወይም ደጋፊ የሆኑ ጥቂት ቡድኖች ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ተገዢነታቸው ለህዝብ ሳይሆን የገዛ ህዛባቸው ጫንቃ ላይ ጭምር ለተቀመጠው መንግሥት ወይም ጎሰኛ ቡድን ነው። ምናልባት ይህን አላስተዋሉት ከሆነ ፈጥነው ሊገነዘቡት ይገባል። የትግራይ ልጆች ብቻ የሚመገቡበት ቤት የትግራይ ልጆች ብቻ የሚገናኙበት ቤት፣ የትግራይ ልጆች ብቻ ከመንግሥት ጋር የሚወያዩበት ኮንፈረንስ አይኑር ማለት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ግን ሁልቀን ወይም ለዘለዓለም በዚያ መልክ እየተሰፋፋ መቀጠሉ ሊያመጣ ወይም ሊያሰጥ የሚችለውን ነገር ማሰብ ይገባል። ይህ ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለወለጋም ለጎንደርም ለጎጃምም ለወሎና ለሌሎችም ሊነገር የሚገባው ነገር ነው። እንዲህ ነኝ ማለቱ ሲበዛ አንተ ግን እንዲህ አይደለህም ማለትን ያመጣል።

ሰዎች ለጎንደር ወይም ለሌላ ልማት ማህበር ሲሰበስቡ ጠቃሚ ዕድርና ልማት ተደርጎ፣ ለትግራይ ልማት ሲሰበሰቡ ግን ፖለቲካ ወይም ጎሰኝነት ተደርጎ መተርጎሙም ራሱን የቻለ አይን ያወጣ ነገር ነው። ዋናው ነገር ግን ይሄ አካባቢንና ጎሳን ብቻ እየለዩ የማልማት ጥማት ጥሩ ቢሆንም “ለደቡብ ህዝብ የአክሱም ሐውልት ምኑ ነው?” ከሚለው የመለስ ዜናዊ ከፋፋይ መርህ ስር ወስዶ እንዳይጥለን ያሰጋል። የአባይ የሶማሌ የኤርትራ ጉዳይ የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ መሆን አለበት። እዚህ ላይ የትግራይን ነገር ደጋግመን ማንሳታችን በመንግሥትም ሆነ በተቃዋሚዎች ተደጋግሞ የሚነገር እንዳለመታደል ሆኖ የሁሉም ዐይን ያረፈበት ሁሉም የፖለቲካ አፉን የሚፈታበት ህዝብ መሆኑን ስላመንን ነው።

ትግሬዎቹ ቤት አትግቡ፣ እነሱ አንድ ናቸው ሁሉም ወያኔ ናቸው ብሎ የሚል ነገር በየቦታው ከመነገርም አልፎ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በደካሞች የሚነገር ደካማ ነገር መሆኑን ልናውቅ ይገበናል። ሁሉም ይለይለት የሚል አጉል ጀብድ ያንን ምንም የማያውቀውን ህዝብ እርስ በርስ ከማስጨረስ በቀር ጀብደኞችን አይነካንም። ፕሮፖጋንዳችን ተሞክሮ ካልሰራልን ነገ ዞረን መታረቃችን አይቀርም። በሙከራው የሚያልቀው ግን ሌላው ህዝብ ነው። ታሪክ ያሳየን ይህንኑ ነው።

ስለዚህ ህዝብ የሚፋቀርበትን አንድ የሚሆንበትን መንገድ ለመፍጠር ከየሳጥናችን የመውጣት ድፍረት ያስፈልገናል። መንግሥትና ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚገዙን ሳንሆን ህግና ፍትህ የሚገዛን ይሁንልን። የሚያለያየን የሚያገለማምጠን ዴሞክራሲ ከሚሆን በዚህ የሚነግዱትን አስወግዶ ሁላችንንም የሚያስተቃቅፈን አገር እንዲኖረን እንሥራ። አራስ ወጣት ሴት፣ የደከመና የታተመሙ አባት አዛውንት አስሮ ማሰቃየት ድል ሆኖ በጀግንንት የሚያስፎክር አይደለም። ይህ ግፍ ሊያስከትለው ከሚችለው ጦስ ለመከላከል በጎሳ ከመቧደን ይልቅ መጀመሪያ ግፉ እንዳይፈጸም ወይም በዚህ እንዲቆም መታገል እንወክለዋለን የምንለውን ህዝብ ሁሉ ነጻ የሚያወጣ መስመር ነው። ካለበለዚያ ግን የሊባኖስና የሂዝቦላህ ነገር ይመጣል። በጦርነት ጊዜ ለያይቶ ማየት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ በርግጥ አለ። እንኳን ተስፋ በተቆረጠበት ቀን ቀርቶ በሰላሙ ጊዜ እንኳ ያንን ቀን ለሚናፍቁ ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን ሥልጣንና ጦርነት ለሚወዱ ወያኔዎችም ያ ቀን በጣም የሚፈለግ ቀን ነው። ብንነቃ ይሻለናል!

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios