ታምራት ላይኔ በኢህአዴግ ተፈተው በጌታ ታሰሩ

የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ዲሴምበር 19/2008 ተፈተዋል። አስራ ሁለት ዓመት ከሁለት ወር ነው የታሰሩት። ለአስራ አንድ ዓመታት ያህል ሰው እንዳያገኛቸው ብቻቸውን አንዲት ክፍል እስር ቤት ውስጥ እንደነበሩም ተናግረዋል።

እኔ ለብቻ ነው የነበርኩት። እንደውም ክፍሏን ለክቻታለሁ። አራት በስምንት የሆነች ጠባብ ኮሪደር ናት። ልፈታ አካባቢ ሁለት ሰው ተጨምሮበት ሶስት ሆነን ነበር። ወደሌላ ቦታ መንቀሳቀስ፣ ከክፍል መውጣት አይፈቀድልንም ነበር። ቤተሰብ ሊጠይቀን ሲመጣ ቅዳሜና እሁድ ነው የምንወጣው። አንዴ ሊጠይቀኝ የመጣ ሰው ዛፍ ይታያሃል ወይ ሲለኝ ከአውሮፕላን ሆድ ሌላ ምንም እንደማይታየኝ መናገሬን አስታውሳለሁ።

አቶ ታምራት ላይኔ በረከት እና ብሌን ታምራት የሚባሉ ሁለት ልጆች አሏቸው። ሁለቱም አሜሪካን አገር ናቸው። ከእስር ቤት ሲወጡ ቤት አልነበራቸውም። “እኔ ቤት ኖሮኝ አያውቅም” እያሉ በቀጥታ እህታቸው ቤት ነበር የሄዱትና እንዲህ አሉ። “ሁሉም ነገር ተቀይሮብኛል። አስራሁለት ዓመት ማለት በጣም ከባድ ነው። ሌላው ቀርቶ የ እህቴ ቤት ተቀይሮብኛል። መፀደጃ ቤት እገባለሁ ብዬ እቃቤት እገባለሁ። ሁሉም ነገር ተቀያይሮብኛል።

አቶ ታምራት ተቀየሩ እንጂ መንግሥት አልተቀየረም። እሳቸው የታሰሩበትም ምክንያት አልተቀየረም። “ያለፈው አልፏል” አሉ “የሚያዋጣኝ የእግዚአብሔር መንገድ ነው” አሉ እንጂ ያሉትን ሁሉ የሚያስተባብል ነገር አልተናገሩም። አቶ መለስ ዜናዊ በወቅቱ “ስኳር አታለላቸው”ብለዋል። አቶ ታምራት ግን የዛሬ አምስት ዓመት እንዲህ ብለዋል፦

ሥልጣኑን የያዘው አካል ለራሱ ፖለቲካዊ ማሻሻጫ ሲል ዜግነታዊና ህገመንግሥታዊ መብቴን ረግጦ የፖለቲካ እስረኛ ሲያደርገኝ ያድነኛል ብዬ የገመትኩት ጠቅላይ ፍርድቤትም ሊረዳኝ አልቻለም። እንዲያውም ሲቀብሩት ብትደርስ አፈር ለግስ” እንደሚባለው የጨቋኞች ተባባሪ ሆኖብኛል።” አቶ ታምራት በዚህ አባባላቸው መንግሥትም ፍርድ ቤትም ያው አንድ ናቸው አሉ።

አቶ ታምራት ላይኔ እስር ቤት የጣላቸው ኢህአዴጋቸውን ትተው ወደ እግዚ አብሄር ሲሄዱ በህዝብ በኩል ነበር ያለፉት። የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲህ ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል፦

በዚያ መራራ ትግል ውስጥ ስሳተፍ መጨረሻው እንዳሰብኩት ይሆናል በሚል አምኜበትና መልካም ተስፋ ሰንቄ፣ ድብቅ አጀንዳና የተሸፈነ ዓላማ ሳይኖረኝ ነበር። ሌላ የጭቆናና የመከራ አዙሪት የሚታይበት ያህ የዛሬው ሥር ዓት ይመጣል ብዬ ጭራሽ አላሰብኩም። የትግሉ መድረሻ የአሁኑ ፍትህ- አልባ ሥር ዓት መሆኑና ለዚህም በመሳሪያነት ማገልገሌ ግን ይፀፅተኛል። ካለፈ በኋላ ቢሆንም እንኳ በዚህ ሁሉ የትግል ውጣ ውረድ ውስጥ ነኝና የተሳሳትኳቸውን ፖለቲካዊ ስህተቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ለማንኛውም የካድኩትን እግዚአብሔርን አምኛለሁ ከማለታቸው ጋር “ወደፊት በዝርዝር በማውጣት የመጪው ትውልድ ማስተማሪያ አደርጋቸዋለሁ።” ያሏቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ነገረውናል። እንደ ወይዘሪት ብርቱካን አንዳች ነገር ተናገሩ ተብለው ተመልሰው ካልታሰሩ የሚያውቁትን ሁሉ ያጫውቱናል የሚል ተስፋ አለ። በኢህዴግ ተፈትተው በጌታ መታሰራቸው ግን ማስገረሙ አይቀርም።

የ54 ዓመቱ ታምራት ላይኔ 5 ዓመት ብቻ በመንግሥትነት ሲቀመጡ 15ቱን ዓመት ጫካ 12ቱን ደግሞ እስርቤት አሳልፈዋል። ሲደመር 27 ዓመት መሆኑ ነው። “ነፍስ ካወቅኩ 18 ዓመቴ በኋላ እንኳ ያለው ቢቀናነስ የመከራው ጊዜ ሳይበልጥ አይቀርም።” ብለዋል።

ያኔ ወስደው ስዊዝ ባንክ አስቀምጠውታል ስለተባለው “ጥቂት” ሚሊዮን ዶላሮች የተባለ ነገር የለም። ስለብዙ ጉዳዮች ሲጠየቁ እየደጋገሙ “በቃ ያለፈው አልፏል ማየትና መነጋገር ያለብን ስለወደፊቱ ብቻ ነው” ካሉ ግን መችስ ምን ይደረጋል? እግዚአብሄር አመላክቶአቸው እስኪነግሩን መጠበቅ ነው። የተከሰሱት በከንቱ መሆን አለመሆኑም ይዋል ይደር እንጂ መታወቁ አይቀርም (ቪዲዮ)

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios