ሁላችንም እንደሌላለው ሀበሻ አይደለንም!

ስዎችን የሚለያየን ነገር እንደበዛው ሁሉ፣ የሚያመሳስለንም አንድ እምነት አለ። ይኸውም ሁላችንም “እኛ እንደ ሌላው አይደለንም” ማለታችን ነው። የእኛ እምነት ከሌላው የተሻለ ነው። እኛ ሀበሾች እንደሌላው ዘር አይደለንም። ሌላው ቀርቶ እኛ ሀበሾች እንደሌሎቹ ሀበሾች አይደለንም። እኔ እንደሌላው ወንድ አይደለሁም። ይገርምሃል እኔ እንደሌሎቹ ሴቶች አይደለሁም። ይህ “እኔና እኛ” ፣ “እንደሌላው አይደለንም” የማለት አባዜ፣ በሁሉም ነገራችን ያለ ልበ ሙሉነት ነው። ይህ ልበ ሙሉነት ወደ ሃይማኖት ሲገባ አክራሪነት፣ ወደ ፖለቲካው ዓለም ሲገባ ደግሞ ግብዝነት እስከመሆን ይደርሳል።

የማንነት ስሜት አስፈላጊና ተፈጥሯዊ ቢሆንም ሌላውም ቤት እንዲህ ያለ ስሜት አለ ብሎ ማሰብንም ይጠይቃል። ካለበለዚያ ዓለምን አጥብቦ አእምሮንም ያጠባል። ብዙዎች ከራሳቸው ጎሳ፣ ከራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲ፣ ከራሳቸው ሃይማኖት፣ ከራሳቸው ጠባብ ክልል፣ አርቀው ማየት የሚያቅታቸው ለዚህ ነው። የኔ ነው ያሉት ወገናቸው ሲሳሳት ሲያዩም ” ባለጌ ነው ቢሆንም የእኛው ባለጌ ነው” እንደተባለው የራስን ወገን ብልግናና ድንቁርናን ስለጥበብ ብሎም ስለ እምነት መቁጠር የተለመደ ነው። ብልግናው ያገዳድልም ጀምሯል።

የኛ አገር መንግሥት ደጋፊዎች ስዎቻቸውን ስለሚደግፉ ብቻ መንግሥት የሚፈጽመው ግድያ ሁሉ “ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ግድያ” መሆኑን ያምናሉ። እንዲያውም “ሟች ከስህተቱ እንዲማር” ህግና ሥርዓት ማስተማሪያ አድርገው እስከመናገር ሲደርሱ የቱን ያህል እንደታወሩ አያውቁትም። ኗሪን ለማስፈራራት ሟችን መግደል ደርግ ላይ ሲሆን “አብዮታዊ” ወንጀል፣ ወያኔ ላይ ሲሆን አብዮታዊ “ዴሞክራሲ” ተደርጎ ይወሰዳል። በዚያኛውም በኩል ቅንጅት ሥልጣን ቢይዝ ማርና ወተት የሚዘንብ የሚመስላቸው ቅንጅትን የኢትዮጵያ ችግር የመጨረሻው ቁልፍ አድርገው በድፍረት ይናገራሉ። ትህትና የተሞላው የእነ ዶ/ር ብርሃኑ መጽሐፍ ግን ይህን አይናገርም። ድርጅቴ በምርጫ አሸንፏልና በዚያም ላይ መሪዎቼ ታስረዋልና መስዋትነትታቸው የመስመራቸውን ዘለዓለማዊ ልክነት መስካሪ ነው የማለትም ልበሙለነት አለ። ይህም ማስቸገሩ አልቀረም።

“ተመርቄያለሁ ብለህ ከተረገመ አትዋል” የሚባለው የአባቶች ተረት ቅንጅትን ከኦነግ ኦነግን ከሻዕቢያ ሻዕቢያን ከሶማልያ እያሰናሰለ የሚሄድ መሆኑ ገና ለገና “ወያኔ ያስብላል” ወይም “ስህተትም ቢሆን የልጆቻችን ስህተት ነው” ተብሎ የሚፈሩት ጥያቄ አያደለም። ብዙ ብዙ ማብራሪያ ይፈልጋል። በሌላም በኩል “ፍቅር በሻዕቢያና በወያኔ እንጂ በቅንጅትና በሻዕቢያ ላይ ግን ያስጠላል” የሚለው የወያኔዎችም ከንቱ ጩኸት፣ በአገር ክህደት ማስከሰሱ የሞኝ ሎጂክ ነው። አገርን በእምነት ጥብቅና ብቻ ሳይሆን ተዋግቶና ሞቶ ማስገንጠል የታየ የተፈጸመ ታሪክ ነው። “እኛ ወያኔዎች እንደ ሌሎቹ ወያኔዎች አይደለንም” የሚሉ አዲስ ወያኔዎች ከሌሉ በስተቀር ይህን መካድ አይቻልም። ወያኔ እንዲህ አድርጓልና ሌላውም ተቃዋሚ ይህንን ያድርግ ማለት ግን “እኛ የምንደግፈው ሻዕቢያ ወያኔ እንደደገፈው ዓይነት ሻዕቢያ አይደለም” የማለትን ጅልነት ያስከትላል። ገና ለገና በአስመራ በኩል አልፈዋል በሚል፣ ቁጣ እና እልህ ያነደዳቸውና በረሃ የወረዱ አርበኞችንም ጥረት፣ እየዘፈነላቸው አሳልፎ በሚሰጣቸው፣ ሞራላቸውን ሊገነባ ሄዶ ሰላይ በሆነባቸው፣ ያንድ ጀምበር ፖለቲከኛ ዝምብለን የምናቀለው ተራ ነገር መሆን የለበትም። በጦርነት መስማማትና አለመስማማት አንድ ነገር ነው። ስዎችን በምርጫቸውና አማራጭ በማጣትም ጭምር የሚወስዱትን እርምጃቸውን ግን ማናናቅ አይገባም። በዚያም በኩልም ቢሆን ገና እውነተኛውን ነገር አላገኘንም።

ስለዚህ ሁሉም ነገር መመዘንና መታየት ያለበት በአገር ላይ ከሆነው ከተደረገውና ሊደረግ ከታሰበው ብሎም ከሚያስከትለው ክብ ውጤት ነው እንጂ “እኛ እንደሌሎቹ አይደለንም የምናደርገውንም እናውቃለን” ከሚል ትእቢት መሆን አይገባውም። እኛኮ ቅንጅቶች ነን ማለት ጥሩ ነገር ነው። ቅንጅት በምርጫው ማሸነፉም እውነት ነው። ያኔ የተመረጠበት ጉዳይ ግን ያሻውን ሁሉ እንዲያደርግበት የተሰጠው ሥልጣን (ማንዴት) ሳይሆን ህዝብ የሚወደውና የሚፈልገውን እንዲያደርግ ብቻ ነው። አሁን የሚደረገው ወይም ሊደረግ ዳር ዳር የሚባለው ነገር ሁሉ፣ ህዝብ የወደደውና የፈለገውን መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት። ከዚያ በፊት ግን ህዝብ የመረጠው ቅንጅት (አመራሩ) ቃል በትክክል የትኛው እንደሆነ ማወቁ የግድ ነው። ቅንጅትን ከተጠያቂነት የሚያድነውም ሆነ ህዝባዊ ታማኘነቱን የሚያስጠብቅለት ይህን “ያልተበረዘውንና ያልተከለሰውን እውነተኛውን የቅንጅት ቃል” ማግኘት ነው። ካለበለዚያ ለአንድ ክርስትና አንድ ሺ ቃል እንደሚያስነግረው እውነተኞቹ ቅንጅቶች እኛ ነን የሚል ነገር እንዳያስከትል ያሰጋል። ያ ደጋሞ ጠቃሚነቱ “ቅንጅት” የሚል ቃል ለሚያባንናቸው ወገኖች ብቻ ነው። ያ ቃል “መንፈስ ነው” እንደተባለው ዛሬ ከስዎች በላይ ሆኗል። ቅንጅት ከፕሮፌሰር መስፍን፣ ከኢንጂነር ኃይሉም ሆነ ከእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በላይ ነው። ራሳቸውን ከዚህ ስም ያስተካከሉ አንዳንድ ስዎች ግን ባልዋሉ ባልተመረጡበትና ራሳቸውን ለአጃቢነትና ጭፍርነት ከአጩበት መድረክ እልፍ ያሉ “የቁም አልጋ ወራሾች” መስለዋል። ግራና ቀኝ ሆነው እንዳቅምቲ ነጋሪት እየተጎሳሰሙ ነው።

ስለሆነም ይህ ካሁን በኋላ ተቃውሞን ያለ ቅንጅት ማሰብ አስቸጋሪ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን “እኔ ቅንጅት እንደ ሌላኛው ቅንጅት አይደለሁም” የሚል ፉከራን ያመጣል። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው የዋነኞቹ የቅንጅት አመራር አካላት ከእሰር መፈታት ነው። እነሱን እንወክላለን የሚለውን የድጋፍ ሰጪውን ጀሌ እብጠትና ያልተገባ ብሎም የተንጠራራ እብሪትን የሚያስወግደውም ይህ ብቻ ነው። ሥራ ተፈቶ የእነሱን የጸብና እርቅን እንቶፈንቶ መስማት ያመጣውም ይህ ውሉ የጠፋ ነገር መኖሩ ነው። የእስልምናውና የክርስትናውንም የመገዳደል ጨዋታም ቢሆን ዋነኞቹና አብዛኞቹ ምን እንደሚሉ መስማት ተገቢ ነው። በቁጥር ትናንሾች የሆኑት የሚፈጽሙት ነገርማ ሁሌም ያው የትናንሾች ነው። እሱን ነው ልብ ማለት። (ዘኢትዮጵያ)

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios