ተስፋ የሚያጣፍጥ ስኳር!

ህብር ስኳር አክስዮን  ፋብሪካ ተሸለመ
“ወደፊት ረሀብን የሚያጠፋው ስኳር ነው!”
ምናልባትም ህብር ስኳር አክስዮን ፋብሪካ የተሸለመው ለዚህ ይሆናል። ኒዮርክ ላይ ሜይ 29 እና 30/2011 የተካሄደው “The International Quality Summit” ህብር ስኳር አክስዮን ማህበርን  ዓለም አቀፍ ተሸላሚ አድርጎታል። ህብር በኢትዮጵያ ግዙፍ የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም ሥራ የጀመረ ማህበር ነው። ፋብሪካው ተገንብቶ ሥራ ባይጀምርም ከወዲሁ ግን ተሸልሟል። ለምን ይሆን? ኦባማ ገና ፕሬዚዳንት እንደሆኑ የተሸለሙትን “የሰላም ኖቤል ሽልማት”  ዓይነት ሳይመስል አልቀረም። “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲባል “የሚያጠግብ ስኳርም” እንዲሁ የተባለ ይመስላል!
“አያያዛችንን ታይቶ ነው የተሸለምነው” ይላሉ አቶ አማረ ለገሠ። “በዚያ ላይ ደግሞ ወደፊት ረሀብን የሚያጠፋው ስኳር ነው።” የሚል ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ደጋግመው ይገልጻሉ። አቶ አማረ የህብር ስኳር አክስዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅና አክሲዮኑን በመሪነት ካደራጁት አንደኛው  ናቸው። በሙያቸው  በ “ሹገር ቴክኖሎጂ ስፔሻላያዝ” ያደረጉ የኬሚካል ኢንጂነር ሲሆኑ በአገሪቱ የስኳር እንደስትሪ ውስጥ ለ 25 ያህል ዓመት አገልግለዋል። በተለይ በመጨረሻው 7 ዓመታት፣ የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ፣ የፋብሪካና የሎጂስቲክ ሥራ አስኪያጅና ከፍተኛ የማኔጅመንት ቲም አባል ነበሩ።
ከሳቸው ጋር አክሲዩኑን ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር የመሠረቱት 30 ሰዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ ስኳር ኢንደስትሪዎች ከ22 እስከ 37 ዓመት በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ በሱፐርቫይዘርነትና በተለያዩ የሙያ ኃላፊነቶች ያገለገሉና የሥራ ልምድ ያካበቱ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
አቶ አማረ ለዘኢትዮጵያ ጋዜጣ እንደገለጹት፣ መተከል አካባቢ ግዙፉን የስኳር ፋብሪካ ለመገንባት የሚንቀሳቀሰው የዚህ ማህበር ፣ዓላማው የስኳር እጥረትን ለመቅረፍ፣ በኤክስፖርት የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት፣ በተጓዳኝና ተረፈ ምርቱ ደግሞ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት፣ ኤታኖልን በአማራጭ ኤነርጂነት ለመጠቀም  ነው።
ጁን 3/2009 የተቋቋመው ህብር ስኳር የአክሲዮን ማህበር፣ 600 ሼር ገዝተው 600ሺ ብር ባዋጡ 30 ሰዎች የተቋቋመ ሲሆን አሁን ወደ 6 ሺ የሚደርሱ ባለ አክስዮኖች አሉት። በዚህም ሽያጩ ወደ 395ሺ ሚሊዮን ብር እንደሚጠጋ ተገልጿል። እንደ አቶ አማረ ገለጻ  የአንዱ የአክሲዮን ድርሻ የሚሸጠው በአንድ ሺብር  ሲሆን “ማህበሩ አሁን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚሆን አክስዮን ለገበያ ማቅረቡን” አስታውቋል።
ስኳር ለምን?
“በዚህን ያህል መጠን ወደ ስኳር ምርት ለመሰማራት ያሰብነው የተለያዩ ምክንያቶች ስላሉን ነው “ያሉት አቶ አማረ “ ለረጅም ዓመታት በመስኩ የሠራን ሰዎች ስለሆን ሥራውን ጥቅሙን፣ ገበያውንና አዋጭነቱን እናውቃለን። አገራችን ውስጥ ስኳር ከየትኛም አንጻር ቢታይ የሚያዋጣ ቢዝነስ ነው። ይህ እንደስትሪ ከገበያውም በላይ ለአገር የሚሰጠው ትልቅ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ አለው” ብለዋል።
ይህንኑ ለማብራራትም የኢትዮጵያን የስኳር ኢንደስትሪ ታሪካዊ መሠረት በመቃኘት ያለውንና የጎደለውን ከሌላው ዓለም ጋር እያነጻጸሩ አብራርተዋል። እንደሳቸው ገለጻ ኢትዮጵያ ውስጥ ስኳር ፋብሪካ የተጀመረው በደቾች በተቋቋመው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ነው። እሱ በተቀቋቋመ በ7 ዓመቱ ደግሞ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ከዚያም 6 ዓመት ቆይቶ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ተቋቁሟል።
ስኳር በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። ድሮ አይታወቅም ነበር። ሁሉም ነገር የሚጣፍጠው በጨውና በማር ነበር። ስኳርን ለህዝቡ ለማስተዋወቅ ፣ በድምጽ ማጉያ “ሀሎ ሀሎ ስኳር ስኳር…” እየተባለ፣ ሻይ በነጻ እየታደለ፣ ህዝቡ እየቀመሰ፣ እንዲጣፍጠውና እንዲያጣጥመው እየተደረገ  የተላመደው በችግር ነው። እንግዲህ ያኔ እንኳ ገበያው ብዙም ባልተስፋፋበት 15 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሶስት ስኳር ፋብሪካ ለመስራት ተችሏል። ዛሬ ስኳር ምን ያህል ተፈላጊ እንደሆነ ይታወቃል። ያም ሆኖ ግን 4ኛውን ፋብሪካ ለማቋቋም እንኳ 21 ዓመታትን ፈጅቷል፡፡ “ስኳር በህዝባችን ተፈላጊ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ስኳርን ለማምረትም በርካታና ልዩ እድል (አድቫንቴጅ) ያለን ነን” ያሉት አቶ አማረ፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ስላላት ብልጫ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።
“ትልቁና ዋነኛው መሬታችን ነው። የኢትዮጵያ መሬት ሸንኮራ አገዳ የማምረት አቅሙ በዓለም ካሉት የላቀ ነው። በአንድ ሄክታር መሬት በመጀመሪያ ቆረጣ ብቻ ወደ 3ሺ ኩንታል የሸንኮራ አገዳ ይቆረጣል። በሌሎች ስኳር አምራች አገሮች ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ብንሄድ የምናገኘው 1ሺ 400 ነው። ትልቁ የስኳር አምራች ብራዚል ብንወስድ ከ1600 እስከ 1700 ኩንታል ነው። እኛጋ ወደ 3ሺ200 ኩንታል አገዳ ይቆረጣል።” በማለት “ይህንን ወንጂ ላይ ስናመርት አይቻለሁ።” ብለዋል።
ሥራ አስኪያጁ “በአንድ ሸንኮራ አገዳ ውስጥ ያለው የስኳር ይዘት ከዓለም አንደኛ” መሆኑን ገልጸዋል። “በአንድ ሸንኮራ ውስጥ ከ13-15 ከመቶ ስኳር ሲኖር ሌሎቹ አገር ሸንኮራ ውስጥ የሚገኘው ከ10 ከመቶ በታች ነው። በሌላ አነጋገር ከአንድ ሄክታር መሬት ከ240 እስከ 260 ኩንታል ሸነኮራ ሲመረት፣ በሌላው አገር የሚመረተው 150 ኩንታል ብቻ ነው። ይሄ ከሌሎች የምርት ዓይነቶችም ጋር ሲነጻጸር የተለየ ውጤት ያለው መሆኑን ያሳያል። ለምሳሌ ጤፍ 30 ኩንታል በቆሎ 60 ኩንታል ብቻ ነው ማምረት የሚቻለው።”
ሽንኮራው ተደጋግሞ የሚቆረጥበትም ጊዜ ሌላው የብልጫው መገለጫ መሆኑን አስረድተዋል። “በኢትዮጵያ አንድ የሸንኮራ አገዳ ቢያንስ ከ5 – 6ጊዜ ይቆረጣል። ሌሎቹ አገሮች ግን ከ3 ጊዜ በላይ አይቆርጡም። ክተወሰነ በኋላ ስኳር ስለማይሰጥ ተነቅሎ መጣልና ሌላ መተከል አለበት። የኢትዮጵያው ግን እየተቆረጠ ራሱን እየተካ ይቆያል።
ለኢትዮጵያ ስኳር ምርት አዋጭነት ሌላው ልዩ ጥቅም ደግሞ የፋብሪካዎች የሥራ ጊዜ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ፋሪካዎች የሚሠሩበት ዘመን ረዘም ያለ ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድ ዓመት ውስጥ በጣም ረጅም ጊዜ በማምረት እንታወቃለን። ምክንያቱም የአየር ጠባያችን ለዚህ ያመቸ ነው። ቀንና ሌሊት እየተሰራ 9 ወር ማምረት እንችላለን። ይህ በየትኛውም አገር አይገኝም። ሌሎቹ 3 ወይም አራት ዓመት ቢሰሩ ነው። የአየር ጠባዩ ከፍና ዝቅ ሳይል የሙቀቱ መጠን ብዙም ሳይዛባ ለ9ወራት መቆየት ይቻላል። ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው። አንድ ትልቅ የስኳር ፋብሪካ ወስደን ኢትዮጵያና አሜሪካ ሉዊዚያና ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ብናቋቋም የኢትዮጵያው 9ወር ሲሰራ የሉዚያናው 3ወር ሠርቶ ብቻ ይቆማል። ደቡብ አፍሪካ ብንወስድ እስከ 5 ወር ሊደርሱ ይችላሉ። ሞርሺየስ 4 ወር አካባቢ ነው። ህንድ እስከ 7 ወር ይሄዳሉ። ይሄ ለኢትዮጵያ ልዩ ጥቅም (አድቫንቴጅ) ነው።
“የሠራተኛ ኃይል እንቀጥራለን፡ ወንጂ 7ሺ፣ መተሐራ 10ሺ ሰው ይሠራል እኛ ወደ 12ሺ ሰው እንቀጥራለን ብለን ነው የተነሳነው።” ያሉት አቶ አማረ ምንም አጠያያቂ ስላልሆነው ስለ ሰው ኃይል ጉልበት ርካሽነትም አብራርተዋል። አቶ አማረ፣ ሌሎቹ ስኳር አምራቾች የሌላቸውን የምርት ወጪ በመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። ከሁሉ የላቀውን ግን “በኢትዮጵያ ስኳር አምራቾች የመሬት ባለቤት መሆናችን ነው” ብለዋል። እዚህ የፋብሪካውም የመሬቱም ባለቤት አንድ ነው። በሌላ ዓለም መሬት ውድ ስለሆነ ከፋብሪካው መገንቢያ 3 እጥፍ ይወደዳል። በዚህ የተነሳ ሌሎቹ ስኳር አምራቾች አገዳውን ከገበሬው ገዝተው ነው የሚሠሩት። አገዳውን ሲገዙ ገበሬው ዋጋውን ጨምሮበት ስለሆነ የሚሸጥላቸው እነሱም ወጪያቸውን አክለውበት መሸጥ አለባቸው። እኛ ግን አሁን አንዱን ሄክታር መሬት ያገኘነው 58 ብር በዓመት ነው። ስለዚህ አገዳውን በገዛንበት ሳይሆን ባመረትንበት ዋጋ እንሰራለን ማለት ነው። በዚያ ላይ የኔን አገዳ አድርስልኝ፣ የኔን አስቀድመህ ፍጭልኝ እያሉ ሌላውን ወገን መጠባበቅ አይኖርም። በተጨማሪም ደግሞ እኛ አገር አንድ ፋብሪካ ከከተማ 150 ኪሎሜትር በራቀ ቁጥር ከ7-8 ዓመት ከታክስ ነጻ ነው። ማበረታቻው አለን። እና 260ሺ ኩንታል በዓመት ለማምረት አቅደናል ስንል፣ ለ8 ዓመት ታክስ ሳንከፍል ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ እናተርፋለን ማለት ነው። አሁን ገንዘብ ኖሮን ገብተን ቢሆን ኖሮ አስበው። ገና ፋብሪካው ውስጥ ሳንገባ ነጻ ነን። ይህ ሁሉ በረከት አለን።
ሥራ አስኪያጁ “እኛ ከእስከዛሬው የስኳር አመራረት ደግሞ ለዬት ያለ ሁኔታ መጠቀም እንፈልጋለን።” ብለዋል። ለምሳሌ ተረፈ ምርቱን (ሞላሰስ) እንደድሮው ወደ መሬት አንጥልም። ኤታኖል ልናመርትበት እንሞክራለን።  አሁን በእቅዳችን መሠረት በመጀመሪያው ዙር 12ሺ ኩንታል ኤታኖል ማምረት እንችላለን። በሚቀጥለው ዙር 15ሺ እያልን ከዚያም በዓመት 28 ሚሊዮን ኩንታል ኤታኖል ለማምረት አቅደናል። የተጨመቀውንም አገዳ እንደማገዶ ቀቅለን ስቲም ተርባይን በመፍጠር፣ በእንፋሎቱ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንችላለን። ለዚህም የተለያዩ መቀቀያዎች( ቦይለሮች)ና ተርባይኖች አሉን። በዚህ ዓይነት በዓመት ወደ 380ሺ000 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይቻላል። ከዚህ ውስጥ ካመነጨነው 60 ሜጋባይት ኃይል 20ውን ለራሳችን ብንጠቀም 40 ለመብራት ኃይል መሸጥ እንችላለን። 217ሺ ሜጋ ዋት ቀላል አይደለም።
“አገራችን ያለው የምግብ ችግር በስኳር ፋብሪካዎች ይቀረፋል!”
ስኳር በዝቶባቸው በሚቸገሩ አገሮችና ስኳር በጎደለባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች መካከል ልዩነት መኖሩ ግልጽ ነው። እንደ አቶ አማረ ማብራሪያ  የኢትዮጵያውያን የነፍስ ወከፍ የስኳር ፍጆታችን 4 ግራም ብቻ ሲሆን የአሜሪካውያን ወደ 100 ግራም ይሆናል። (ቁጥሩ አከራካሪ ቢሆንም ልዩነቱ ግን እጅግ ብዙ ነው) ምንም እንኳ አሜሪካውያን 75 እና 80 ዎቹ አማካይ እድሜዎች ውስጥ እየኖሩ ዘጠናና መቶ ለመድፈን ቢጨነቁም፣ ስኳር የሚሰጠውን በቂ ኃይልና ጉልበት አግኝተዋል። እኛ አገር ግን ባነሰ ስኳር ተጠቃሚነት ከብዙ በሽታዎች ጋር የምንሞተው ገና በ40 ዎቹ እድሜ ውስጥ ነው። በዚያ ላይ አቅምና ጉልበት ያንሰናል። እነሱ ብዙዎን ጉልበት የሚያገኙት ከስኳር ነው። እነሱ ስኳርን ቢወቅሱ አጣጥመውና ጠግበው ነው። ስኳር  አወሳስዱ ሊለያይ  ቢችልም፣  ተፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ግን ተጠቃሚ ከሆኑ አገሮች መረዳት እንችላለን።
እኛ ከስኳር ከሻይ የዘለለ ስኳር አንፈለገውም። ስኳር ቅመም እንጂ ምግብ ያልሆንበት አገር ነው ያለን። የገበያ እጥረት ሳይሆን የስኳር እጥረት ነው ያለው። አሁን በኢትዮጵያ እጥረት አለ። የሚመረተው ከ2.8 ሚሊዮን እስከ 3 ሚሊዮን ኩንታል ነው። የሰውን ፍላጎት እንዳለ ነው ዋጋ ደግሞ አሻቅቧል። ከዚህ ያላነሰም ዋጋ ለማረጋጋት ተብሎ ተገዝቶ ገብቷል። ግን ይህም ሆኖ ዋጋውን ሊያወርደው አልቻለም። ዛሬ ስኳር በኩንታል ከ1200 እስከ 1400 ብር ድረስ ይሸጣል። ይህ መሆን አይገባውም።  ስኳር ለማምረት ከውጭ የሚጠይቀው ብዙ ግብ አት አይኖርም። ሁሉንም ማለት በሚያስችል መልኩ አገር ውስጥ አለን። ስለዚህ እኛ ይህን ሁሉ የመለወጥ አቅም በመፍጠር መሥራት እንችላለን።
እንዲያውም ካገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን በውጭ ከሌሎች አገሮች ጋር ተወዳዳሪ የመሆን ስትራቴጂክ ጠቀሜታም አለን። አገራችንም ያለችበት ቅርበት ለአረብና አውሮፓ አገሮች የተመቸ ነው። እነዚህ አገሮች ከፍተኛውን ስኳር ተጠቃሚዎች ናቸው። ከእነብራዚልም ሆነ ደቡብ አፍሪካ ጋር በመርከብ ርቀት እንኳ  ብንወዳደር እኛ ለአካባቢዎቹ ቅርበን ነን። የመጨረሻ ዝቅተኛ ዋጋ ያለው ስኳር ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታል። የትኛውም አገር የዝቅተኛ ዋጋ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታል።
ይህን ሁሉ ነገር በማገናዘብ፣ ዘርፈ ብዙ የሆነ ጥቅም ለማስገኘት፣ በመዘጋጀቱ ለዓለም አቀፍ ሽልማት መብቃቱን የህብር ኃላፊ ገልጸዋል። “ጥራት ባለው ሁኔታ አምርተን የምንሄድ መሆኑን ከወዲሁ አምነውበታል።” ቢዝነስ ኢኒሼቲቭ  ስፔይን አገር ያለ ድርጅት ነው። በዓለም ያሉ ፋብሪካዎችን በተለያዩ እያየ ይሸልማል። ትልቅ ተስፋን መያዙን የሚገልጸው የዚህ አክስዮን ማህበር ባለድርሻ (የሼር ባለቤት) ለመሆን እያንዳንዳቸው 1ሺ የኢትዮጵያ ብር የሆኑ ከ10 ሼሮች ጀምሮ መግዛት እንደሚቻል ከሥራ አስኪያጁ ገለጻ መረዳት ተችሏል።  በእያንዳንዱ ሼር 7 ከመቶ የአገልግሎት ዋጋ (ብር 70) ፕሪሚየም ይከፈላል። ከተገዛው ሼር ቢያንስ 50 ከመቶው ከምዝገባው ጋር ወዲያ ሲከፈል ሌላው በኋላ የሚከፈል እንደሆነም ተመልክቷል። የተሸጠው ሼር  የተገዛበት ዋናው ገንዘብ እስካሁን የሚቀመጠው  በዝግ አካውንት ሲሆን፣ ይህም የሚንቀሳው ሼሩን የገዛው ሰው በፈቀደበት ጊዜ ይሆናል። አክስኪዮን ማህበሩም እስካሁን የሚንቀሳቀሰው ለሥራ ማስኬጃ አገልግሎት ለሚከፈለው በፕሪሚየሙ መሆኑን አብራርተዋል።
በመጨረሻም፣ ይህን ለአገር ተስፋ የሚጣልበትን፣ ባለ ትልቅ ራዕይ ፕሮጀክት፣ ባለቤትና የጥቅሙም ተካፋይ ለመሆን፣ በየአገሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ የህብር ስኳር አክስዮን ማህበርን ሼር በመግዛት ተካፋይ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። ለዓመታት ያገለግልን ባለሙያዎች፣ መሬት፣ ምቹና ልዩ የተፈጥሮ ሀብት፣ ተከፍቶ ከሚጠብቀን ትልቅ ገበያ ጋር ፣እድሉ እያለን ኢትዮጵያውያን ሙሉ ለሙሉ ተሳታፊ የማንሆንበት ምክንያት አይታየኝም ብለዋል። እሳቸው እንዳሉትም መጪው ዘመን የስኳር ይመስላል። ተስፋ የሚያጣፍጥ ስኳር ! (ዘኢትዮጵያ)

Leave a Reply

Photo Gallery

Designed by Nebxstudios